ከሽግግር በኋላ በሚመሰረተው የሱዳን መንግስት ውስጥ አልሳተፍም- አል ቡርሃን
በሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግና ምርጫ ለማካሄድ ለሱዳናውያንና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቃል ገብተናል ብለዋል
በተቃዎሞ ሰልፍ ላይ ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች የሱዳን ጦር ኃላፊነት እንደማይወስድ አስታውቀዋል
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን፤ ከሽግግር በኋላ በሱዳን በሚመሰረተው አዲስ መንግስት ውስጥ ተሳተፎ እንደማይኖራቸው ተናገሩ።
ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን፤ በሱዳን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሽግግር ለማድረግ እና ምርጫ ለማካሄድ ለራሳቸው፣ ለሱዳን ህዝብ እና ለዓለምቀፉ ማህበረሰብ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል።
“ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ቁርተኛ ነን” ያሉት ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን፤ “ሽግግሩን ሊያደናቅፍ ከሚችል ከማንኛውም ጣልቃገብነት ለመጠበቅ ቃል እንገባለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን አክለውም፤ ከስልጣን የተነሱትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀጣይ 24 ሰዓታት ውስጥም አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ቃለ መጠየቅ የተላለፈው በርካታ ሱዳናውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞዋቸውን በሚያሰሙበት ወቅት ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለተቃዎሞ አደባባይ ወጥተው ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች የሱዳን ጦር ኃላፊነት እንደማይወስድ አስታውቀዋል።
“የሱዳን ጦር ንጹሃን ዜጎችን አልገደለም” ያሉት አልቡርሃን፤ “አሁን በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው፤ ከምርመራው በኋላ ምን እንደተፈጠረ የምናይ ይሆናል” ብለዋል።
ገለልተኛ የሆነ የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ ባወጣው መረጃ ከሆነ በሱዳን የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ300 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ ከትናት ጀምሮም የቀጠሉ ሲሆን፤ በርካታ መምህራን በካሩቱም በሚገኘው የትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ ፊት የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውም ተነግሯል።
ሱዳን የመምህራን ማህበር ባወጣው መረጃም በትናትናው ሰልፍ ላይ ቢያንስ 80 መምህራን መታሰራቸውን አስታውቋል።