የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በኢትዮጵያ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረግ ጥረትን እንደሚቃመዉ ገለጹ
አቶ ደመቀ ከዲሞክራቲክ ኮንጎው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
ኮንጎ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የአፍሪካ ህብረትን እና አህጉሩን ይጎዳል ብላለች
የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቴሽኬዲ፤ በኢትዮጵያ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረግ ጥረትን እንደሚያወግዙ አስታወቁ፡፡
ፌሊክስ ቴሽኬዲ፤ የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ ምንም አይነት ድርድር እንደማያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ይህንን ያሉት፤ በሀገራቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ በኩል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ከአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ ጋር በአዲስ አበባ ተወያተዋል፡፡
አቶ ደመቀ እና ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና የአፍሪካ ህብረት የመፍትሄው አካል በመሆን ሊጫወቱት የሚችለውን ሚና በተመለከተ መወያየታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ቴሽኬዲ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ ለአቶ ደመቀ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንት ትሺሴኬዲ አጋርነትንና ወንድማማችነትን ለማሳየት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሰላም መምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነትን ለማሳየት ከፍተኛ የባለስልጣናት ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል ተብሏል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል ስልጣን ለመያዝ እና የግዛት አንድነትን እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማጋጨት የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ በጽኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የአፍሪካ ህብረትን እና አህጉሩን ይጎዳል ብላ እንደምታምንም የሀገሪቱ ባለስልጣን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የኮንጎ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላም ጥረት ለመደገፍና ለማበረታታት ያደረጉትን ተነሳሽነት ማድነቃቸው ተገልጿል፡፡
አቶ ደመቀ፤ በግጭቱ ውስጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ከሁለቱም ማለትም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ማየት የምትፈልጋቸውን ጉዳዮች ለኮንጎው ባለስልጣን ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሌሎች የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የሰብአዊ መብት ተኩስ አቁም አዋጅ ቢያውጅም ህወሃት ይህንን ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን እንዲገነዘቡም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአጎራባች ክልሎች ያለውን ግጭት እያሰፋና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ እያራዘመ ያለውን ህወሃትን እንድታወግዝ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡