አልጄሪያ ለሞሮኮ ነዳጅ ማቅረብ አቆመች
አልጄሪያ “ሞሮኮ ሉአላዊ አንድነቴን ያላከበረ የጥላቻ ተግበራትን ፈጽማለች” በሚል ነው የነዳጅ አቅርቦቱን ያቋረጠችው
አልጄሪያ በቅርቡ ከሞሮኮ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ አየር ክልሏን ዝግ ማድረጓ ይታወሳል
አልጄሪያ በጎረቤት ሀገረ ሞሮኮ በኩል በማስተላፊያ ቧንቧ አማካኝነት የምታደርገው የነዳጅ ንግድ እንዲቋረጥ አዘዘች።
ውሳኔው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተፈጠሩ የመጡ አለመግባባቶችን ተከትሎ የመጣ እንደሆነም የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
“ሞሮኮ አልጄሪያን በተመለከተ የሀገሪቱን ሉአላዊ አንድነት ያላከበረ የጥላቻ ተግበራትን ፈጽማለች” ያሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በሞሮኮ በኩል የሚደረጉ የነዳጅ ንግዶች ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም “ሶናትራክ” የተባው የአልጄሪያ ነዳጅ አውጪ ኩብንያ ከሞሮኮው “ኦኔ” የኤሌክትሪክ ኩብንያ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ ፕሬዝዳቱ አዘዋል።
የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ሰፔን የሚያስተላልፈው “የማግሪብ- አውሮፓ” የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላፊያ ቧንቧ በሞሮኮ በኩል የሚያለፍ ሲሆን፤ ለዚህም ሞሮኮ ከአልጄሪያ የምታገኘው ክፍያ እንዳላት ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ሞሮኮ ከአልጄሪያ ከሚነሳው የተፈጠሮ ጋዝ በመጠቀም ከሀገሪቱ ፍላጎት 10 በመቶ የሚሆነውን የኤልክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ትጠቀማለች።
በአልጄሪያ እና በሞሮኮ መካከል የነበረው የተፈጠሮ ጋዝ አቅርቦት ስምምነት ትናንት እሁድ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የአልጄሪያ ባለስልጣናት ኮንትራቱን ለማደስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋልም ነው የተባለው።
“ሶናትራክ” የተባው የአልጄሪያ ነዳጅ አውጪ ኩብንያ ለስፔን የሚያቀርበውን የተፈጥሮ ጋዝ “ሜድጋዝ” በተባለ ማስተላፊያ ቧንቧ በኩል ማስተላፉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
“ሜድጋዝ” ማስተላለፊያ ቧንቧ በባህር ስር የሚሄድ ሲሆን፤ የሚፈለገውን ያክል የተፈጠሮ ጋዝ ለስፔን ላያቅርብ ስለሚችል አቅሙን የማሳደግ ስራ መስራት የሚያስፈልገው መሆኑም ተነግሯል።
አልጄሪያ እና ሞሮኮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ ጉዳች ላይ ወደ አለመግባባት እያመሩ ሲሆን፤ አልጄሪያ በቅርቡ ከሞሮኮ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧ እና የሞሮኮ አውሮፕላኖች በአየር ክልሏ እንዳይበሩ መከልከሏ ይታወሳል።
አልጄሪያ ሞሮኮ የአልጄሪያ ተገንጣዮችን ትደግፋለች በሚል እና የእስራኤልን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ባለስልጣኖቼን ትሰልላች ስትል ራባትን ትከሳለች።