አልጄሪያ ስራ ለሌላቸው ዜጎቿ ወርሃዊ ድጎማን የምትሰጥ ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሀገር ያደርጋታል
አልጄሪያ በሥራ አጥነት-ጥቅማ ጥቅሞች መርሃ ግብር ስራ ለሌላቸው ዜጎቿን በየወሩ ልትደጉም መሆኑ ተሰምቷል።
የነዳጅ ላኪ ሀገራት (ኦፔክ) አባል የሆነችው አልጄሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የነዳጅ ዋጋ መናር ለወጣት ስራ አጥ ዜጎቿን በየወሩ እንደትደጉም ይረዳታል የተባለ ሲሆን፤ ድጎማው በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የማህበራዊ ቀውስ ያስታግሳል ተብሏል።
በሥራ አጥነት-ጥቅማ ጥቅሞች መርሃ ግብር እድሜያቸው ከ19 እስከ 40 መካከል ያሉ 580 ስራ ፈላጊዎች ወርሃዊ ክፍያ እንደሚያገኙም ነው ብሉምበርግ የዘገበው።
በዚህም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ስራ ፈላጊ አልጄሪያውያን በየወሩ 13 ሺህ የአልጄሪያ ዲናር ወይም 91 የአሜሪካ መቀበል ይጀምራሉ ተብሏል።
የ25 ዓመቱ ሰይድ ፋታህ በባዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ ለ5 ዓመታት ስራ አጥ ሆኖ መቆየቱን ይናገራል፤ የሀገሪቱ መንግስት የመጀመረው ድጎማ የሚበረታታ ነው ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ቤተሰቦቹን ለመርዳት በጥሩ ደመወዝ ስራ መያዝን እመርጣለሁ ይላል።
የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለመሆን ከ1 ሚሊየን በላይ አልጄሪያውያን አመልክተዋል የተባለ ሲሆን፤ ለድጎማው በቂ ለመሆን አመልካቹ ከማንኛውም ድርጅት ጋር የስራ ውል የሌለው፣ ከሌላ የእርዳታ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ያልሆነ እና ያገባ ከሆነም የትዳር አጋሩ ቋሚ ገቢ የሌለው/የሌላት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቃል ተብሏል።