አሊባባ ቻትጂፒቲን የሚፎካከር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ይፋ አደረገ
የቻይናው ኩባንያ “ቶንጂ ሽዌን” የሚል ስያሜ የሰጠውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በቅርቡ ስራ እንደሚያስጀምር ገልጿል
የአሜሪካው ቻትጂፒቲ በአጭር ጊዜ ተቀባይነትን ማግኘት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አምሳያውን መፍጠር ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉ ይነገራል
የቻይናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አሊባባ የአሜሪካውን ቻትጂፒቲ የሚፎካከር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስራቱን ይፋ አድርጓል።
“ቶንጂ ሽዌን” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቻትጂፒቲ የሚሰጠውን አገልግሎት ሁሉ ይሰጣል ተብሏል።
በአሊባባ ቢዝነስ ላይ ስራ ይጀምራል የተባለው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በይፋ አገልግሎት የሚጀመርበትን ጊዜ ግን ኩባንያው አላሳወቀም።
“ቶንጂ ሽዌን” በግርድፉ “በሺዎች ለሚቆጠሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ” የሚል ትርጉም እንዳለው ሬውተርስ ዘግቧል።
በቻይንኛ እና እንግሊዝኛ አገልግሎት ይሰጣል የተባለው “ቶንጂ ሽዌን” በአሊባባ የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ “ዲንግቶክ” ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ዳኔል ዣንግ ተናግረዋል።
አሊባባ የ“ቶንጂ ሽዌን” ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ አማዞኑ አሌክሳ በድምጽ ምላሾችን እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
“ቶንጂ ሽዌን” ንግግርን ወደ ጽሁፍ መቀየር፣ የኢሜል መልዕክቶችን የመጻፍና የቢዝነስ ንድፎችን የማዘጋጀትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ይሰጣልም ነው የተባለው።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ህዳር ወር ላይ የአሜሪካው ኦፕን አይ ኩባንያ ቻትጂፒቲን ይፋ ካደረገ በኋላ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ላይ ተጠምደዋል።
ማይክሮሶፍት፣ ጎግል፣ የቻይናው ባይዱን ጨምሮ ቢሊየን ዶላሮችን ያፈሰሱባቸውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችም ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ይህ የቴክኖሎጂ ፉክክርም በህግ ማሰሪያ ካልተበጀለት አደገኛ ነው ያሉ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት መመሪያዎችን እያወጡ ነው።
የትዊተር ባለቤቱ ኤለን መስክም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፉክክር ጤናማ አይመስልም፤ “ሰብአዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ካሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መሪዎች አንዱ ነው።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ጎልድማን ሳች በቅርቡ ባወጣው ጥናት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የ300 ሚሊየን ሰዎችን ስራ ሊተካ እንደሚችል ማመላከቱ የሚታወስ ነው።