ድምጽን በመስማት ብቻ ጉንፋንን የሚለየው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ
በህንድ ተመራማሪዎች የተስራው ቴክኖሎጂ ጉንፋን ይዞኛል በሚል ከቢሮ ለመውጣት የሚደረግ ሙከራን ከንቱ ያደርጋል ተብሏል
ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ወደህክምና ተቋማት በመሄድ የሚባክን ጊዜ እና ገንዘብን እንደሚያስቀርም ነው የተነገረው
የህንድ ተመራማሪዎች ጉንፋን የያዘውን ሰው በድምጹ ብቻ መለየት የሚያስችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን አስተዋወቁ።
የሳርደር ቫልባቢ ብሄራዊ የቴክኖሎጂ ተቋም በ630 ጀርመናውያን ላይ ጥናት አድርጓል።
ከጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥ 110ሩ ጉንፋን ያመማቸው ነበሩ የሚለው የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ፥ ድምጽ እና ጉንፋን ያላቸው ትስስር በጥናቱ መዳሰሱን አብራርቷል።
የድምጽ መጎርነን ብቻውን የጉንፋን ምልክት አይደለም የሚሉት የኤሌክትሪክ ኢንጂነር ፓንካጂ ዋርሉል፥ ጉንፋን ሲይዘን የድምጽ መርገብገብና ሌሎች ለውጦች እንዳሉ አብራርተዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ከ1 እስከ 40 ቁጥር እንዲጠሩና በሳምንቱ መጨረሻ ያከናወኑትን በአጭሩ እንዲያብራሩ ተደርጓል።
ይህም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሳሪያው ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ የተሳታፊዎቹ የድምጽ ሞገድ ከጉንፋን ጋር ያለው ዝምድና በጥልቀት ተጠንቷል።
ቀደም ብሎ የጤነኛ ሰዎች ድምጽ ሞገድን ጉንፋን ከያዛቸው እንዲለይ የሰለጠነው ሰው ሰራሽ አስተውሎትም በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥ በትክክልም ጉንፋን የያዛቸውን ለይቷል ተብሏል።
የቴክኖሎጂው ስኬታማነትም የ70 በመቶ ውጤት ተሰጥቶታል ይላል የኢኮኖሚስት ዘገባ።
የሰው ሰራሽ አስተውሎቱ ሰዎች ስልክ በመደወል ብቻ ጉንፋን ይያዝ አያዛቸው ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
ይህም ወደ ህክምና ተቋማት በማምራት የሚባክን ጊዜ እና ገንዘብን ያስቀራል ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ።
አንዳንድ ሰዎችም ጉንፋን አሞናል በሚል ከስራ ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ከንቱ ያደርግባቸዋል፤ በቢሮ ውስጥ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በርግጥም በጉንፋን መያዝ አለመያዛቸውን ማረጋገጥ ስለሚቻል።
የህንድ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት ቴክኖሎጂ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ እያበረከተ ያለው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።