አልጄሪያ የብሪክስ አባል ለመሆን ማመልከቷን አስታወቀች
የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ኢኮኖሚዋን ለማስፋፋትና እንደ ቻይና ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ትሻለች
ከ40 በላይ ሀገራት ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው ተነግሯል
አልጄሪያ የብሪክስ ቡድንን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን እና በ1.5 ቢሊዮን ዶላር የቡድኑ ባንክ የአክሲዮን ባለቤት ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቦዩን አስታውቀዋል።
ቴቦዩን በቻይና ጉብኝታቸው ማብቂያ ላይ እንደተናገሩት አልጄሪያ ብሪክስን በመቀላቀል አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን ለመክፈት ጥረት ታደርጋለች።
ሮይተርስ እንደዘገበው የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር በነዳጅ እና ጋዝ ሀብት የበለጸገች ሲሆን፤ ኢኮኖሚዋን ለማስፋፋት እና እንደ ቻይና ካሉ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ትፈልጋለች።
ብሪክስ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የያዘ ሲሆን፤ ኢትዮጽያም የዚህ ቡድን አባል ለመሆን ጠይቃለች።
ቡድኑ ከ40 በመቶ በላይ የዓለምን ህዝብ እና 26 በመቶውን የዓለም ኢኮኖሚን ይሸፍናል።
"ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ አመልክተናል። በባንክ ውስጥ ባለአክሲዮን አባል ለመሆን ደብዳቤ ልከናል። አልጄሪያ ለባንኩ የመጀመሪያዋ መዋጮ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል" በማለት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከ40 በላይ ሀገራት ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።
አርጀንቲና፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩባ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኮሞሮስ፣ ጋቦን እና ካዛኪስታን ፍላጎት ካላቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።