ተወዳዳሪው ከውድድሩ የታገደው የእስራኤል ተጋጣሚውን አልገጥምም በማለቱ ነው
አልጀሪያው የጁዶ ተወዳዳሪ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ታገደ። የ30 ዓመቱ ፈቲህ ኑሪን ሀገሩን ወክሎ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ73 ኪሎ ግራም የጂዶ ውድደር አይነት ለመወዳደር ወደ ጃፓን አቅንቶ ነበር።
ይህ ተወዳዳሪ የፊታችን ሰኞ ከሱዳኑ መሀመድ አብደላርሱል ጋር የጁዶካራቲ የውድድር ፕሮግራም ነበረው።ይሁንና ይህ አልጀሪያዊ ከዚህ ሱዳናዊ ተወዳዳሪ ጋር ከተጫወተ በኋላ በቀጣይ የእስራኤል አቻውን እንደሚገጥም ይጠበቅ ነበር።
እስራኤል ከፍልስጤም ጋር ባለባት የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ይህ አልጀሪያዊ የእስራኤል አቻውን ላለመግጠም ሲል ከሱዳኑ ተወዳዳሪ ጋር እንደማይጫወት ለአወዳዳሪዎቹ አሳውቋል።በዚህም ምክንያት ይህ አልጀሪያዊ ተወዳዳሪ ከውድድሩ እንዲታገድ መወሰኑ የተገለጸ ሲሆን ወደ አልጀሪያም ከሰሞኑ እንዲመለስ ይደረጋል ተብሏል።
የኑሪን አሰልጣን ውድድሩን ከስፍራው ለመዘገብ ወደ ቶኪዮ ካቀናው የአልጀሪያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቆይታ “እኛ በውድድር እጣ አወጣጡ ላይ እድለኞች አይደለንም የእስራኤሉን ተወዳዳሪ ጋር ተደልድለናል በዚህ ምክንያትም ከውድድሩ ራሳችንን አግለናል ትክክለኛ ውሳኔ ወስነናል” ሲል ተናግሯል።
ዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ የአልጀሪያ ተወዳዳሪው የወሰነውን ውሳኔ ከኦሎምፒክ የውድድር መርህ እና ከስፖርት ፍልስፍና የተቃረነ ነው ሲል ተቃውሟል።
በዚህም ምክንያት ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን እንደሚመረምር ሲያሳውቅ የአልጀሪያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ደግሞ ተወዳዳሪውን እና አሰልጣኙን ወደ አገራቸው እንደሚልኩ አሳውቀዋል።
ዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን አልጀሪያ ስፖርት ከማንኛውም ፖለቲካ፤ዘረኝነት እምነት እና ፕሮፓጋንዳ ነጻ ነው የሚለውን ህግ በመጣሷ ቅጣት እንደሚጠብቃት ያስጠነቀቀ ሲሆን ምርመራው እንደተጠናቀቀ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ገልጿል።
ከዚህ በፊት በተካሄዱ የኦሎምፒክ ውድድሮች የኢራን እና የግብጽ ስፖርተኞች ከእስራኤል አቻ ተወዳዳሪዎቻቸው ጋር ለመወዳደር እንደማይፈልጉ አሳውቀው ያውቃሉ።
ለአብነትም በ2019 የፈረንጆች ዓመት በጃፓን በተካሄደው ውድድር ኢራን ከአስራኤል አቻዋ ጋር አዘልወዳደርም በማለቷ ምክንያት የአራት ዓመት እገዳ በዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን እገዳ ተላልፎባት ነበር።