ሁሉም አካላት ግጭቱን ከማባባስ ይታቀቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዩክሬኑ ቀውስ ላይ አስተያየት ሰጡ
ተመድ ሩሲያን የሚያወግዝ የውሳኔ ሀሳብ በትናንትናው እለት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉም አካላት ሁኔታው እንዳይባበስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት በዩክሬን ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ግጭቱን ከማባባስ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች የቅርብ ጦርነት ትዝታ ውስጥ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ሁኔታው እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ከነበረችበት ጦርነት የምታስተምረው ብዙ ጭብጥ አለ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት በቤተሰብ፣ በማህበረብ እና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ውድመት ልምዳችን አሳይቶናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት የሚተካ ቢሆንም በማህበረሰቡ ላይ ግን ዘላቂ ጠባሳ የሚጥል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጋራ የተገነቡት አለምአቀፍ ድርጅቶችና አለምአቀፍ ህግጋት የማግለያ ቦታ መሆን የለባቸውም፤ምክንያቱም የተቋቋሙት ችግር ለመፍታት እና ለላቀ ዲፕሎማሲያዊ ነው ብለዋል፡፡
የሩሲያ እስካሁን ባካሄደችው ዘመቻ በደቡብዊ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር ችላለች፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምእራበውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማእቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው እለት ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
የውሳኔ ሀሳቡ በ143 የድጋፍ ድምጽ፣35 ተአቅቦ እና በ5 ተቃውሞ ሩሲያ ከዩክሬን ለቃ እንድትወጣና ተኩስ እንድታቆም የሚያስጠነቅቀዉን የዉሳኔ ሀሳብ አጸድቋል።ቻይና እና ህንድ ድምጸ ተአቅቦ ካሰሙ ሀገራት ውስጥ ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።
ከተጀመረ አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ጦርነት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዩክሬናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። የሩሳያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ውይይት ጀምረዋል።