የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሩሲያ “ልታጠፋን ነው” ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲፈጸም ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ጦራቸው ኬርሰንን መቆጣጠሩን አስታወቁ።
የሩሲያ ጦር በደቡብ ዩክሬን የምትገኘውን ኬርሰንን መቆጣጠሩን ዛሬ ገልጿል። ከተማዋ የጥቁር ባህር እና ዲኒፐር ወንዝ ወደብ የሚገኝባት በመሆኗ ስትራቴጂያዊ እንደሆነች ይነገራል።
ምንም እንኳን የሩሲያ ጦር ከተማዋን መቆጣጠሩን ቢያስታውቅም የአካባቢው ባለስልጣናት ግን ይህንን አስተባብለዋል። ባለስልጣናቱ ከተማዋ አለመያዟን የገለጹ ሲሆን፤ በሩሲያ ጦር መከበቧ ግን ተናግረዋል ነው የተባለው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር የሩሲያው አቻቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍሉ ዝተዋል። ባይደን ንግግር ሊያደርጉ ሲሉ በአሜሪካ የዩክሬን አምባሳደር አቀባብል ተደርጎላቸው ከባለቤታቸው ጋር ተቀምጠው ነበር።
ምንም እንኳን አሜሪካና አጋሮቿ ፑቲን ላይ ቢዝቱም የሩሲያ ጦር ግን ዘመቻውን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል። እስካሁን በተወሰደ መረጃ መሰረት ከ450 ሺህ በላይ ዜጎች ከዩክሬን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል ተብሏል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የሩሲያ ዓላማ ዩክሬንን ማጥፋት እንደሆነ እየተናገሩ ነው።
የሩሲያ ሰራዊት ብረት ለበስ የጦር ተሸከርካሪዎችን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ እያስጠጋ መሆኑም እየተገለጸ ነው። በዩክሬንና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ሙሉ የዓለምን ትኩረትም አግኝቷል።
አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን መጣላቸውን ቀጥለዋል።
ሩሲያ የመጨረሻ ያለችውን የኒዩክለር ጦሯን በተጠንቀቅ እንዲቆም ካዘዘች በኋላ ዓለም ጦርነቱን ከመታዘብ አልፎ ስጋት አድሮበታል ተብሏል።