ማዕቀብና መግለጫ በዝቷል ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ናቸው ጦሩ የጸረ ኑክሌር ኃይሉን በበለጠ ተጠንቀቅ ላይ እንዲያደረግ ያዘዙት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጸረ ኑክሌር ኃይላቸው በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን አዘዙ፡፡
ፑቲን ከገቡበት የዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ከምዕራባዊ ሃገራት ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ነው ጦሩ በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ እንዲሆን ያዘዙት፡፡
ዛሬ እሁድ ከከፍተኛ ባለስልጣናቶቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆኑ ሃገራት ጠንከር ያለ መግለጫ እያወጡ መሆኑንና ማዕቀቦችን እየጣሉ በመሆኑ ጸረ ኑክሌር ኃይሉ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን አዘዋል፡፡
ትዕዛዙ ለሃገሪቱ ጦር አመራሮች የተሰጠ ነው፡፡
ይህ ሁኔታውን የበለጠ እንዳያባብሰውና ወዳልተፈለገ አስከፊ የኑክሌር ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል፡፡
ፑቲን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ማዕቀብን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን በሚወስዱና ጣልቃ በሚገቡ ሃገራት ላይ ጠንከር ያለ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
የአየር እና የነዳጅ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት በዩክሬን በመፈጸም ላይ የሚገኘው የሩሲያ ጦር ወደ ሁለተኛዋ ትልቅ የዩክሬን ከተማ ካርኪቭ መግባቱን ዛሬ አስታውቋል፡፡