ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቤላሩስ ድንበር ለመነጋገር ተስማማች
የፕሬዝዳንቱ የአቋም ለውጥ የሩሲያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት የፈጠረው ተጽእኖ ሳይሆን እንዳልቀረ እየተነገረ ነው
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከሰአታት በፊት "በቤላሩስ የምናደርገው ድርድር የለም" ማለታቸው አይዘነጋም
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቤላሩስ ድንበር ለመነጋገር ተስማማች፡፡
ከሰአታት በፊት በሌሎች ሀገራት ካልሆነ ዩክሬን እንድትጠቃ ግዛቷንም ጭምር በፈቀደችው ቤላሩስ ውስጥ ከሩሲያ ጋር የምንነጋገርበት ምክንያት የለም ሲሉ የነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አሁን ላይ ውሳኔያቸው መቀልበሳቸው እየተሰማ ነው፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ ዜሌንስኪ በቤላሩስ ድንበር ለመነጋገር ተስማምቷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሰአታት ውስጥ የአቋም ለውጥ እንዴት አሰዩ ለሚለው በምክንያትነት የተቀመጠ ግልጽ ነገር ባይኖርም፤ የሩሲያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት የፈጠረው ተጽእኖ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
ሩሲያ ቀደም ሲል የተለያየ ስብጥር ያለው ልዑክ ለድርድር ወደ ቤላሩስ መላኳ አስታውቃ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ወደ ቤላሩስ ያቀናው የሩሲያ ልዑክ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ ተደራዳሪ አካላትን መያዙን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል፡፡
ለድርድሩ ስኬታማነት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉም የሩስያ ጠንካራ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ቃል ገብተዋል፡፡
ጦርነቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀልብ እንደሳበ ቀጥሏል፡፡ ሩሲያ ሉዓላዊ ሃገር የሆነችውን ዩክሬንን ወራለች በሚል ድርጊቱን የሚያወግዙት አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊ አጋሮቿ የተለያዩ የማዕቀብ ናዳዎችን በሞስኮው ላይ እያዘነቡ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸው የጸረ ኑክሌር ኃይሉን ከምን ጊዜውም በላይ እንዲያዘጋጅ ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡
የአየር እና የነዳጅ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት በዩክሬን በመፈጸም ላይ የሚገኘው የሩሲያ ጦር ወደ ሁለተኛዋ ትልቅ የዩክሬን ከተማ ካርኪቭ መግባቱን ዛሬ አስታውቋል፡፡
ዩክሬን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICJ) አቤት ማለቷን ፕሬዝዳንቷ አስታውቀዋል፡፡ ሩሲያ ጅምላ ጭፍጨፋን ተገን አድርጋ በፈጸመችብን ወረራ መጠየቅ አለባትም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡ ወረራውን እንድታቆም የሚያስገድድ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀናልም ብለዋል ዘሌንስኪ ጉዳዩ በመጪው ሳምንት መታየት ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ በማስታወቅ፡፡