በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ወስነው የነበሩት 6 የእንግሊዝ ክለቦች ውሳኔያቸውን ሻሩ
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲና ቶትንሀም ናቸው ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉት
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር የዓለም እግር ኳስን ለመታደግ የመጣ ነው
በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ወስነው የነበሩት ስድስት ታላላቅ የእንግሊዝ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ውሳኔያቸውን በመሻር ራሳቸውን ከውድድሩ ውጭ አደረጉ።
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ቶትንሀም ናቸው በአዲሱ አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ለመሳተፍ ወስነው የነበሩት።
ክለቦች አሁን ላይ ውሳኔያቸውን መሻረቸው የተነገረ ሲሆን፤ ማንቸስተር ሲቲ ውሳኔውን በመሻርና ራሱን ከአዲሱ አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር በማግለል የመጀመሪያው ክለብ መሆኑም ታውቋል።
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ የማንቸስተር ሲቲ ውሳኔን በመከተል ራሳቸውን ከአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ውጭ ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ክለቦቹ ከአዲሱ አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር መውጣታቸውን አስመልክቶ ምን አሉ
ማንቸስተር ሲቲ ይፋዊ በሆነ መንገድ ከአዲሱ አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ለመውጣት በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ሊቨርፑልም ከአውሮፓ ሱፐር ሊግ ጋር የነበረው ግንኙነት ይፋዊ በሆነ መንገድ መቋረጡን አስታውቋል።
ማንቸስተር ዩናይትድም ከደጋፊዎች፣ ከእንግሊዝ መንግስት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶችን በጥሞና በመከታተል በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ላይ ላለመሳተፍ ከውሳኔ መድረሱን ገልጿል።
አርሴናል በበኩሉ ለደጋፊዎች በይፋ በጻፈው ክፍት ደብዳቤ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ በደብዳቤውም ስህተት መስራቱን እና አሁን ላይ ደጋፊዎችን በመስማት አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ለመውጣት ሂደት መጀመሩን አመላክቷል።
የቶትንሀም ፐሬዚዳንት ዳኒኤል ሌቪም የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድርን አስመልክቶ በተላለፈው ውሳኔ መፀፀታቸውን አስታውቀዋል።
ቼልሲ ባሳለፍነው ሳምንት ከተቀላቀለው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ራሱን ለማግለል ይፋዊ በሆነ መንገድ እየሰራ መሆኑን አረጋግጧል።
የክለቦችን ውሳኔ በተመለከተ እየተሰጡ ያሉ ምላሾች
የአውሮፓ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ዩ.ኢ.ኤፍ.ኤ) ፐሬዚዳንት ሌክሰሳንደር ካፌሪን ስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች ከአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመውጣት መወሰናቸው መልካም ነገር ነው ብለዋል።
ክለቦች አሁን ወደ ነበሩበት ማእቀፍ ተመልሰዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በአንድነት በመሆን ወደፊት የተሻለ ነገር መስራት ይቻላል ሲሉም አስታውቀዋል።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በትዊተር ገጻቸው፤ የክለቦቹ ውሳኔ እንዳስደሰታቸው እና ክለቦቹ ከውሳኔው ላይ እንዲድርሱ ያስቻለውም የእግር ኳስ ደጋፊዎች፣ የእግር ኳስ ክለቦች እና የሀገሪቱ ማህበረሰብ በጋራ የሰሩት ስራ ነው ብለዋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ስድስቱን ክለቦች ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው ምለሽ፤ የሱፐር ሊግ ውድድር ቅርጽን እንዳዲስ ለማደራጀት እንደሚሰራ አስታውቋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ሊቀ መንበር እና የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፈሎሬንቲኖ ፔሬዝ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር የዓለም እግር ኳስን ለመታደግ የመጣ ነው ብለዋል።
ምክንያቱም በእግር ኳስ ላይ ባለው የጥራት ችግር አሁን ያለው ወጣቱ ትውልድ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር በጣም የቀነሰ ነው፤ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ግን ይህንን ያስተካክላል ሲሉም ተሰምተዋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የውድድር ቅርጽ ምን ይመስላል
አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ 20 ተሳታፊ ቡድኖችን የሚያካትት ሲሆን፤ የውድድሩ ተሳታፊ 20 ቡድኖችም በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ የሚጫወቱ ይሆናል።
ከሁለቱ ምድቦች ከአንድ እስከ ሶስት ሆነው የሚጨርሱት ቡድኖች ለሩብ ፍጻሜ የሚያልፉ ሲሆን፤ ከየምድቦች አራተኛና አምስተኛ የሚወጡ ክለቦች ደግሞ እርስ በርስ ተጋጥመው አሸናፊው ሩብ ፍጻሜውን የሚቀላቀል መሆኑንም የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እቅድ ያመላክታል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ እንደሚጀመር በወጣው መርሃ ግብር ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹም የሳምንቱ አጋማሽ ላይ እንደሚደረጉም ተጠቅሷል።