ስድስት ታላላቅ የእንግሊዝ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአዲሱ ሱፐር ሊግ ለመሳተፍ ተስማሙ
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል ፣ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲና ቶትንሀም በሱፐር ሊግ ውድድሩ ይሳተፋሉ
አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ 20 ተሳታፊ ቡድኖችን ያካተተ ሲሆን፤ በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ ይጀመራል
አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሊቨርፑል ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ቶትንሀም በአዲሱ አውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ለመሳተፍ ከተስማሙ 12 ክለቦች ውስጥ ተካተቱ።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ለመሳተፍ የወሰኑት ታላላቅ የእንግሊዝ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችም ከጣልያኖቹ ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ እንዲሁም ከስፔን ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይቀላቀላሉ።
መስራች ቡድኖቹ በየሳምንቱ ግማሽ ላይ ጨዋታዎቹን ለማድረግ መስማማታቸውን እና በሀገራቸው የሊግ ጨዋታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንደሚቀጥልም የአውሮፓ ሱፐር ሊግ አስታውቋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድርን ለመጀመርም ወደ ሊጉ የሚቀላቀሉ ሶስት ክለቦች በመጠበቅ ላይ ሲሆን፤ ሊጉን የሚቀላቀሉት ቀሪ ክለቦችም በቅርቡ ይታወቃሉ ተብሏል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የወንዶች ውድድር ከተጀመረ በኋላም በተቻለ ፍጥነት የሴቶች ውድድር እንደሚጀመርም አዲሱ ሊግ አስታውቋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የውድድር ቅርጽ ምን ይመስላል
አዲሱ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ 20 ተሳታፊ ቡድኖችን የሚያካትት ሲሆን፤ 12ቱ መስራች ክለቦች በቅርቡ የሚቀላቀሉ ሶስት ክለቦች እንዲሁም 5 ክለቦች ደግሞ ተወዳድረው የአውሮፓ ሱፐር ሊግን ይቀላቀላሉ።
የሊጉ ውድድር ተሳታፊ 20 ቡድኖችም በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ የሚጫወቱ ሲሆን፤ ከሁለቱ ምድቦች ከአንድ እስከ ሶስት ሆነው የሚጨርሱት ቡድኖች ለሩብ ፍጻሜ የሚያልፉ ይሆናል።
ከየምድቦች አራተኛና አምስተኛ የሚወጡ ክለቦች ደግሞ እርስ በርስ ተጋጥመው አሸናፊው ሩብ ፍጻሜውን የሚቀላቀል መሆኑንም የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እቅድ ያመላክታል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ እንደሚጀመር በወጣው መርሃ ግብር ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹም የሳምንቱ አጋማሽ ላይ እንደሚደረጉም ተጠቅሷል።
አዲሱን ሊግ በተመለከተ እየተሰጡ ያሉ ምላሾች
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ወሬ በትናንትናው እለት መሰማቱን ተከትሎ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንሲትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውሳኔውን ማውገዛቸው ተሰምቷል።
ዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) በበኩሉ ለአዲሱ የሊግ ውድድር እውቅና አለመስጠቱን ገልጾ፤ በዚህ ጨዋታ ላይ የሚሳተፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫ ላይ የመሳተፍ እድል እንደማይሰጣቸውም አስታውቋል።
የአውሮፓ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ዩ.ኢ.ኤፍ.ኤ) በበኩሉ በአውሮፓ ሱፐር ሊግ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ከሁሉም የሀገር ውስጥ ውድድሮች በአውሮፓም ሆነ በዓለም መድረክ በሚካሄዱ ውድድሮች ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በበኩሉ አዲሱ ውድድር ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በተሻለ መልኩ ገንዘብ እንደሚያስገኝ በማስታወቅ፤ ተሳታፊ ክለቦችም ጠቀም ያለ ትርፍ ያገኙበታል ብሏል።