“ሁሉም የታተመው ገንዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳተመው ህጋዊ ገንዘብ ነው” ዶ/ር ይናገር ደሴ
ለህገወጦች የብር ቅያሬው አስቸጋሪ እንደሆነባቸው እና ህብረተሰቡም እንዳይተባበራቸው ጥሪ ቀርቧል
ባለፉት 5 ቀናት ብቻ 65 በመቶ በሚሆኑ የንግድ ባንኮች ቅርንጫፎች አዲሱ የብር ኖት መሰራጨቱ ተገልጿል
“ሁሉም የታተመው ገንዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳተመው ህጋዊ ገንዘብ ነው” ዶ/ር ይናገር ደሴ
ኢትዮጵያ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ የብር ኖቶችን ካስተዋወቀችበት ጊዜ ጀምሮ የብር ኖቶቹ ወደ ንግድ ባንኮች እየተሰራጩ በአሮጌው በመቀየር ላይ ናቸው፡፡
እስካሁን ያለውን የአዲሱን የብር ኖት ስርጭት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) “እስካሁን የብር ኖቱ ለውጥ በጥሩ ሁኔታ እየሔደ ነው” ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ባጠቃላይ ከሚገኙ 6,064 የሁሉም የንግድ ባንኮች ቅርንጫፎች ባለፉት 5 ቀናት በመላ ሀገሪቱ በ3,964 ቅርንጫፎች (65 በመቶ) ስርጭት እንደደረሰም ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በመላ ሀገሪቱ “እስካሁን 40 ቢሊዮን ብር ገደማ ተሰራጭቷል” ያሉት ዶ/ር ይናገር አዲሱን ብር ከማሰራጨት በተጨማሪ አሮጌዉንም የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ እና በዚህ ሂደት የጸጥታ አካላት ጥብቅ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ህጋዊና ህገወጥ ገንዘብን ከመያዝ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ በማህበረሰቡም ይሁን በጸጥታ አካላትም ዘንድ የተሸለ ግንዛቤ መፈጠሩንም ነው የገለጹት፡፡ ማብራሪያ ከመሰጠቱ በፊት የትኛውንም መጠን ገንዘብ ከግለሰቦች ላይ በህገወጥነት ስም የመውረስ ድርጊት የተስተዋለ ሲሆን የእንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ “የጸጥታው ዘርፍ አመራሮች ዝርዝር መልዕክት አስተላልፈዋል” ብለዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከአዲሱ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ህገወጥ ገንዘብ ያለ በማስመሰል መረጃዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብ “በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ እየተሰራጨ የሚገኘው ገንዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳተመው አዲስ ገንዘብ ነው ፤ ሌላ ገንዘብ የለም” ያሉት ዶ/ር ይናገር “ሁሉም የታተመው ገንዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳተመው ህጋዊ ገንዘብ ስለሆነ ህብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ አንዳች ጥርጣሬ ሊኖረው አይገባም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ አንዳንዴ በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ነገሮች እንደሚነሱ ያወሱት ዶ/ር ይናገር “ይህ የሚጠበቅ እና አስቀድመንም እንደሚኖር የገመትነው ነው” ብለዋል፡፡ ይሁንና በመላ ሀገሪቱ እየተሰራጨ የሚገኘው ብሔራዊ ባንኩ ያሳተመው ህጋዊ ገንዘብ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በድጋሚ ተናግረዋል፡፡
ከገንዘቡ ስርጭት ጋር በተያያዘ እስካሁን የተከናወነው ስርጭት ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት አንጻር ትልቅ ስኬት እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ለየባንኮቹ የተሰራጨው የገንዘብ መጠን እንደሚለያይ በመግለጽ “ተጨማሪ ገንዘብ የሚፈልጉ ባንኮች ካሉ መጥተው እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል“ም ነው ያሉት፡፡
አጠቃላይ ስርጭቱን በሚመለከት ባንኮች ሙሉ ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ እንደሚገኙ በማንሳት “አንዳንድ ባንኮች እኛ ከምናሰራጨው በተጨማሪ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም ወደ ቅርንጫፎቻቸው በመድረስ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ትልቅ እገዛ እያደረጉልን ነው“ ብለዋል፡፡
በኤቲኤም ማሽኖችም ሙሉ በሙሉ የአዲሱ ገንዘብ አገልግሎት እንዲጀመር ባንኮች የሚፈልጉትን ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ የብዙ ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖቻቸው እንደሚሰሩ እና ከማሽኖች ጋር ተያይዞ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ተስተካክለው አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ እንዲከናወን ከሁሉም የባንክ ፕሬዝዳንቶች ጋር በጥብቅ መነጋገራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የብር ኖት ቅያሬው ከታቀደው የ3 ወራት ጊዜ ቀደም ብሎም ሊጠናቀቅ እንደሚችል ዶ/ር ይናገር ገልጸዋል፡፡
“ለህገወጦች የብር ቅያሬውን አስቸጋሪ አድርገንባቸዋል“ ያሉት ዶ/ር ይናገር ማንም ሰው የራሱን ገንዘብ ብቻ ወደ ባንክ በማስገባት እና ህገ-ወጦችን ባለመተባበር የብር ቅያሬው ያስፈለገበት ምክንያት እንዲሳካ ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችም በህገወጥ መንገድ የዉጭ ምንዛሪዎችን ባለማድረግ መሰል ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡