እስራኤል በሀማስ ላይ አዲስ ዘመቻ መክፈቷን ተከትሎ 90 በመቶ የጋዛ ነዋሪዎች ከመኖርያቸው መፈናቀላቸው ተሰማ
ከሰሞኑ በተጀመረው የምድር ላይ ጥቃት አጠቃላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 2 ሚሊየን ተጠግቷል
የመንግስተቱ ድርጅት የጋዛ ነዋሪዎች በየትኛውም ስፍራ ከጥቃት ነጻ አይደሉም ብሏል
እስራኤል በሀማስ ላይ አዲስ ዘመቻ መክፈቷን ተከትሎ 90 በመቶ የጋዛ ነዋሪዎች ከመኖርያቸው መፈናቀላቸው ተሰማ።
እስራኤል በባለፈው ሳምንት በጋዛ የጀመረችውን አዲስ የምድር ላይ ጥቃት ተከትሎ ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 1.9 ሚሊየን መድረሱ ተሰምቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተበበርያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው መረጃ አሁን ላይ ሁሉም የጋዛ ነዋሪዎች በሚባል ደረጃ መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡
እንደ ቢሮው መረጃ በጋዛ 2.1 ሚሊየን ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1.9 ሚሊየን ሰዎች ሲፈናቀሉ ይህም ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ 90 በመተውን የሚሸፍን ነው፡፡
አዲሱን ዘመቻ ተከትሎ በአስር ቀናት ውስጥ ተጨማሪ 80ሺ ሰዎች ተፈናቅለዋል ያለው ኦቻ በአሁኑ ወቅት በጋዛ ንጹሀን እራሳቸውን ከጥቃት የሚከላከሉበት ምንም አይነት ከውግያ ነጻ ቀጠና የለም ብሏል፡፡
በግንቦት ወር እስራኤል በራፋ በከፈተችው የአየር እና የምድር ጥቃት 1.7 ሚሊየን ሰዎች ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን፤ የአየር ላይ ጥቃቱ ከሰሞኑ ጋብ ቢልም የተፈናቃዮች ቁጥር አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ በ200ሺ ጨምሯል፡፡
የእስራኤል ጦር የሹጃያን መንደር ጨምሮ በጋዛ ሰርጥ በተለያዩ አካባቢዎች በአዲስ መልክ በጀመረው በታንክ የታገዘ የእግረኛ ጦር ጥቃት የሀማስ ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረስኩ ነው ሲል ገልጿል፡፡
የሀማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እያሽመደመደ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚገልጸው የእስራኤል ጦር ሀማስ ጠፍቶባቸዋል ባላቸው ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ጋዛ 3ኛ ዙር ሲል የጠራውን አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በባህር ዳርቻዋ ከተማ ኑስርያት የሚገኙ ተፈናቃዮች እራሳቸውን ከአየር ጥቃት ለመከላከል የአሽዋ ግንቦችን በመስራት ላይ ሲሆኑ በስፍራው ከፍተኛ የምግብ እና የንጹህ መጠጥ ውሀ እጥረት በመኖሩ ተፈናቃዮች የባህር ውሀ ለመጠጣት መገደዳቸውን ኦቻ አስታውቋል፡፡
በሀማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ከዛም በዘላቂ ጦርነት ማቆም ላይ ሁለቱ ወገኖች እንዲነጋገሩ የሚጠይቀውን አሜሪካ ያዘጋጀችውን የስምምነት ሀሳብ ሃማስ በዛሬው እለት ስለመቀበሉ ሮይተርስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በመንግስታቸው እና በዜጎቻቸው ዘንድ በጋዛው ጦርነት በሚያሳልፉት ውሳኔ ከፍተኛ ጫና የበረታባቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአሜሪካ የድርድር ጥያቄ ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጡ ሀማስን ሳላጠፋ ጦርነት አላቆምም በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡
9ወራትን ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት እስካሁን ከ38 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ87 ሺህ የሚልቁት ደግሞ የተለያየ አይነት መጠን ያለው ጉዳት አስተናግደዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመሰረታዊ እርዳታ አቅርቦት እጥረት ከጦርነቱ ያልተናነሰ የሞት አደጋ በጋዛውያን ላይ ማንዣበቡን አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።