እስራኤል በካን ዮኒስ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
በጋዛዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ከትላንት ጀምሮ አካባቢውን ለቀው መውጣት ጀምረዋል
ከሰሞኑ በደቡባዊ ጋዛ በርከት ያሉ የእስራኤል ታንኮች መታየታቸው አዲስ የምድር ላይ ዘመቻ ልታከናውን ስለመሆኑ ፍንጭ ሰጥተዋል
እስራኤል በጋዛ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ በሆነችው ካን ዮኒስ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠች፡፡
ከትላንትናው እለት ጀምሮ በከተማዋ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የአየር ላይ ጥቃት ቀዝቀዝ ወዳለባት ራፋ ለመጓዝ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡
በደቡባዊ የጋዛ ክፍል በአዲስ መልክ የተጀመረውን አዲስ ጥቃት ተከትሎ እስካሁን 8 ሰዎች ሲሞቱ ከ30 የሚልቁት ደግሞ መቁሰላቸው ተሰምቷል፡፡
የምድር ላይ ዘመቻው የተጀመረው በካን ዮኒስ አካባቢ ከሃማስ ጋር በትብብር ይዋጋል የሚባለው ኢስላሚክ ጃሀድ የተሰኝው ታጣቂ ሮኬት ወደ እስራኤል መተኮሱን ተከትሎ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የእስራኤል ጦር 20 ሮኬቶች ከካን ዮኒስ መተኮሳቸውን እና አብዛኞቹን ማክሸፍ መቻሉን ነው ያስታወቀው፡፡
የካን ዮኒስ ነዋሪዎች በእጅ ስልኮቻቸው ላይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የድምጽ መልዕክት እንደደረሳቸው የተናገሩ ሲሆን አልማዋሲ ወደ ተሰኘው በእስራኤል ጦር ቁጥጥር ስር ወደ ሚገኝው ስፍራ እንዲያቀኑ እንደተነገራቸውም ነው የገለጹት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራኤል አዲስ የጀመረችው የምድር ላይ ዘመቻ በጋዛ ለንጹሀን ደህንነት ዋስትና የሚሆን ምንም ስፍራ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
በሃማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት የንጹሀንን ህይወት መቅጠፉን አያቆሙም ያሉት ዋና ጸሀፊው ፍልስጤማውያን ከጥቃት የሚደበቁበት ምንም አይነት ስፍራ በጋዛ የለም ብለዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦሩ ሀማስን ለማጥፋት መቃረቡን በገለጹበት በትላንትናው ንግግራቸው ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
2.3 ሚሊየን የጋዛ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ሲሆን በአከባቢው በቂ እርዳታ አለመድረስ ከፍተኛ ረሀብን ሊያስከትል እንደሚችል የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
ከ8 ወራት በላይ በዘለቀው የጋዛ ጦርነት እስካሁን 37 ሺህ 900 ንጹሀን ህይወታቸውን ሲያጡ ከ80 ሺህ የሚልቁት ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
አሜሪካ እና የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የአለም መሪዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ተደርጎ ጦርነቱ እንዲቋጭ ጥሪ ቢያቀርቡም ሁነኛ መፍትሄን ገቢራዊ ማድረግ ተስኗቸው ጦርነቱ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡