ሳኡዲ አረብያ ከአዲሱ የኢራን አስተዳደር ጋር በቅርበት እሰራለሁ አለች
በቅርቡ ወዳጅነታቸውን ያደሱት ሀገራት ለአመታት በየመን ጦርነት በእጅ አዙር ሲዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል
ሳኡዲ አረብያ ከአዲሱ የኢራን አስተዳደር ጋር በቅርበት እሰራለሁ አለች።
የሳኡዲ ልኡል አልጋ ወራሽ ሞሀመድ ቢን ሰልማን ለአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳነት መሱድ ፔዝሽኪያን የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት ልከዋል፡፡
አልጋወራሹ በፔዝሽኪያን አስተዳደር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት እና የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በቀጠናዊ የበላይነት ሽኩቻ በየመን ለአመታት በእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ የከረሙት ሁለቱ ሀገራት ባሳለፍነው አመት መጋቢት ወር ላይ በቻይና አደራዳሪነት በተደረገ ውይይት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማምተዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ አምባሳደሮችን ከመለዋወጥ ባለፈ ግንኑነታቸውን ለማደስ የተለያዩ የሁለትዮሽ ጉባኤዎችን በተደጋጋሚ አድርገዋል፡፡
ሳኡዲ ለዘብተኛ ናቸው በሚባሉት መሱድ ፔዝሽኪያን የስልጣን ዘመን ደግሞ ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር ከአስተዳደሩ ጋር በቅርበት እስራለሁ ብላለች፡፡
የኢራን እና ሳኡዲ አረብያ ቀጠናዊ ፉክክር መነሻ ምንድን ነው?
በእስራኤል እና ግብጽ መካከል ከተፈረመው ከ1978ቱ የካምፕ ዴቬድ ስምምነት ወዲህ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስከበር ግብጽ ፣ እስራኤል እና ሳኡዲ አረብያን መርጣለች፡፡
ይህን መሰረተ በማድረግ ከእነዚህ ሀገራት ጋር በወታደራዊ ፣ በጦር መሳርያ ሽያጭ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች ብርቱ ወዳጅነትን መስርታለች፡፡
ወትሮም ቢሆን ከምእራቡ አለም ጋር የቀረበ ወዳጀነት የሌላት ቴሄራን የሪያድን ከዋሽንግተን ጋር መደመር አለወደደችውም፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በስልጣኔ ፣ በታሪክ የበላይነት እንዲሁም በሺአ እና በሱኒ ሙስሊሞች መካከል ባለ ፉክክር ለአመታት የዘለቀው ውጥረት በ2011 ከተቀሰቀሰው የአረብ ጸደይ እኩል አብሮ ፈንድቷል፡፡
ሞሀመድ ቢንሰልማን ከአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ጋር በትብብር ማሳካት የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በርካታ ሀገራት በህዝብ አመጽ ሲናጡ እና የተለያዩ መንግስታት መቀያየር ሲጀምሩ ተጽእኗቸውን ለማሳረፍ በግልጽ መሻኮት የጀመሩት ሀገራቱ በየመን በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በእጅ አዙር ተዋግተዋል፡፡
ከየመን ባለፈ በኢራቅ ፣ ሊባኖስ እና ሶሪያ ሁለቱ አካላት ተጽእኗቸውን ለማንበር የሚያግዛቸውን የየራሳቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይከተላሉ፡፡
በእነዚህ ሀገራት ፖለቲካ ውስጥ ጽንፈ የሆነ ፍላጎት ያላቸው ሀገራቱ ወዳጅነታቸው ይጸና ዘንድ በአቋማቸው ላይ መቀራረብ ይፈልጋሉ።
በቅርቡ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ኢብራሂም ራይሲ በ2021 ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትኩረት አድርገው ሲቀሰቅሱባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የሀገራቸውን ቀጠናዊ ተጽእኖ ማረጋገጥ እንዱ ነበር፡፡
ሪያድ እና ተሄራን ግንኙነታቸውን ለማደስ ከተስማሙበት የመጋቢቱ ድርድር በኋላ መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም አሁንም ግን መሰረታዊ በሚባሉ ግንኙነታቸው ዙርያ የረጋ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡
ከነዚህ መካከል የወጭ ንግድ ፣ የፋይናንስ ትብብር ፣ የውጭ ግንኙነት እና በቀጠናው በሚፎካከሩባቸው ሀገራት ያላቸውን ፍላጎት ለማስታረቅ የሄዱበት ርቀት እምብዛም አልተሻገረም፡፡
የሳኡዲ ልኡል አልጋ ወራሽ ሞሀመድ ቢን ሰልማንም ለዘብተኛ ናቸው ከሚባሉት አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ጋር ማሳካት ከሚፈልጓቸው አጀንዳዎች መካከል በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የቀጠናው ተንታኞች ጽፈዋል፡፡