ለ97 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ከ1 ወር በፊት የተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ የቸልተኝነት ዉጤት ነው ተብሏል
በፓኪስታን ከ 3 ፓይለቶች አንዱ በሀሰት የአብራሪነት ፈቃድ እንደሚሰሩ ተገለጸ
በፓኪስታን ከ30 በመቶ በላይ (1/3ኛ) የሚሆኑት የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች ሀሰተኛ የአብራሪነት ፈቃድ ይዘው እንደሚሰሩ የሀገሪቱ የአቪዬሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ ጉላም ሳርዋር ክሀን እንዳሉት 262 የአውሮፕላን አብራሪዎች የበረራ ፈተናዎችን ያልወሰዱና በምትካቸው በህገወጥ መንገድ በክፍያ ሌሎች ግለሰቦች እንዲፈተኑላቸው ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ አብራሪዎች የበረራ ልምድም የሌላቸው መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ መረጃ ይፋ የተደረገው በአውሮፓውያኑ መጋቢት 22 በሀገሪቱ ደቡባዊ ከተማ ካራቺ ተከስክሶ 97 ሰዎች የሞቱበት አደጋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በተደረገበት ወቅት የሪፖርቱ አካል ተደርጎ ነው፡፡ ይሁንና የተከሰከሰው አውሮፕላን ፓይለት የአብራሪነት ፈቃዱ ሀሰተኛ ይሁን አይሁን አልተገለጸም፡፡
በሪፖርቱ እንደተገለጸው የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪዎች ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጣቸውን መመሪያ ችላ ብለው በወቅቱ ስለ ኮሮና ቫይረስ መረጃ ሲለዋወጡ ነበር፡፡
አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት የበረራ ከፍታው ለማረፍ የሚያስችለው ባለመሆኑ አብራሪዎቸቹ አውሮፕላኑን እንዳያሳርፉ በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሶስት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ቢነገራቸውም ማስጠንቀቂያውን አለመቀበላቸው ተገልጿል፡፡
አብራሪዎቹ ይባስ ብለው የማረፊያ ጎማዎችን ሳያዘጋጁ አውሮፕላኑን ለማሳረፍ ሲያንደረድሩ እንደነበር እና በዚህ አጋጣሚ የአውሮፕላኑ ኤንጂኖች ችግር እንዳጋጠማቸው ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በኋላ አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን መልሰው ወደ አየር ሊያወጡ ቢሞክሩም ኤንጂኖቹ በመጎዳታቸው ምክንያት ሊታዘዛቸው ባለመቻሉ አሳዛኙ አደጋ በቸልተኝነት እንደተከሰተ ነው የተብራራው፡፡
በፓኪስታን በአሁኑ ወቅት 860 አብራሪዎች በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከሀገሪቱ አየር መንገዶች አንዱ የሆነው የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ከካራቺው አደጋ ክስተት በኋላ ባደረገው ማጣራት በሀሰተኛ የአብራሪነት ፈቃድ የሚሰሩ አብራሪዎቹን ከስራ ማገዱን የሲኤንኤን ዘገባ ያሳያል፡፡
ይሁን እንጂ የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ አብዱላህ ክሀን እንዳሉት ሀሰተኛ የበረራ ፈቃድ ያላቸው አብራሪዎች በሀገሪቱ በሚሰሩ ሌሎች አየር መንገዶችም የሚገኙ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡