የግድቡን መገንባት የደገፈው ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮኮስ ማነው?
ግድቡ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ የኤሌክትሪክ ኃይልን እንድታቀርብ ከማስቻልም በላይ አዎንታዊ ቀጣናዊ ተጽዕኖች አሉት
ኮኮሱ አሜሪካና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋንያን የ2015ቱን የመርሆዎች ስምምነት እንዲያከብሩም አሳስቧል
አሜሪካ የ2015ቱን የመርሆዎች ስምምነት እንድታከብር ኮኮሱ አሳሰበ
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሁሉንም አካላት ቀጣይነት ያለው ትብብር እና ሰላማዊ ውይይቶችን እንደሚያበረታታ ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮኮስ አስታወቀ፡፡
ውይይቶቹ በጋራ ተጠቃሚነት፣ መተማመን እና አለም አቀፍ ህግጋት ላይ ሊመሰረቱ ይገባል ያለው ኮኮሱ ግድቡ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ የኤሌክትሪክ ኃይልን እንድታቀርብ ከማስቻልም በላይ አዎንታዊ ቀጣናዊ ተጽዕኖች እንደሚኖሩት ገልጿል፡፡
አሜሪካና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋንያን ሶስቱ ተደራዳሪ ሃገራት በካርቱም የፈረሙትን የ2015ቱን የመርሆዎች ስምምነት እንዲያከብሩም ነው ያሳሰበው፡፡
ሚናቸውን ያለ አድልዎ እንዲቀጥሉ እና ከአፍሪካ ህብረትና የቀጣናውን ሁኔታ ጠንቅቀው ከሚያውቁ ዲፕሎማቶች ጋር ብቻ እንዲመክሩም የጠየቀም ሲሆን ህብረቱ በዋናነት ሰላማዊ ስምምነቶች ለጥቂት የአህጉሪቱ ሃገራት ብቻም ሳይሆን ለሁሉም እንደሚበጁ በመግለጽ ትልቅ ሚናን ሊጫወት እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ኮኮሱ ግድቡ ተደጋጋሚ ድርቅ ለሚያጠቃው የአፍሪካ ቀጣና ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋልም ነው ያለው፡፡
በድርቅ እና በአንበጣ መንጋ በደረሰበት ጉዳት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊጋለጥ እንደሚችል በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ምድር እየተገነባ ያለው ግድብ ለግብጽ የውሃ አቅርቦትን በማሻሻልና የናይል ውሃ ጫናን በመቀነስ፣ ለሱዳን የውሃ ቁጥጥር ስርዓቷን ለማዘመንና ደለልን ለማስቀረት ይጠቅማል እንደኮኮሱ ገለጻ፡፡
የግብርና ፕሮጄክቶችን ለማስፋት የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ እና ጎርፍን ለመከላከል እንደሚረዳም አስቀምጧል፡፡
የግድቡን መገንባት የደገፈው ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮኮስ ማነው?
ኮኮሱ እ.ኤ.አ በ1971 ነው የተቋቋመው፡፡ የአሜሪካ ህገመንግስት ያጎናጸፈውን መብት፣ ስልጣን እና የፌዴራል መንግስቱን በጀት በመጠቀም ለአፍሪካ አሜሪካውያን መብት መጠበቅ ይሰራል፡፡ መገፋት ከሚደርስባቸው አናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች ጎን ይቆማልም፡፡
መሰል የፖሊሲ ጉዳዮችን እያነሳ ሲታገልም ያለፉትን 48 አመታት ዘልቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች እና ኮንግረስ የተውጣጡ እና 82 ሚሊዬን አሜሪካውያንን የወከሉ 55 አባላት አሉት፡፡ ከጠቅላላው አሜሪካ ህዝብ 25 በመቶ ያህሉን የሚወክሉት አባላቱ 17 ሚሊዬን አፍሪካ አሜሪካውያንንም ይወክላሉ፡፡ ከዴሞክራት ፓርቲ አባላት መካከል አንድ አራተኛ ያህሉም የዚሁ ኮኮስ አባላት ናቸው፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ግድቡን በተመለከተ የያዘው አቋም ትክክል እንዳልሆነ እና አድሏዊ አካሄድን እንደሚከተል አጥብቀው ሲሞግቱ የነበሩ የኔቫዳውን የምክር ቤት አባል ስቴቨን ሆርስፎርድን መሰል ታላላቅ ፖለቲከኞች በኮኮሱ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት አሉበት፡፡
ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ የህግ አውጭ ምክር ቤት አባል ኤልሃን ኦማርም በዚሁ ስብስብ ውስጥ ትገኝበታለች፡፡
መግለጫውን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ምን አሉ?
ከአሁን ቀደም አሜሪካ በድርድሩ በነበራት ሚና እምብዛም ደስተኛ እንዳይደሉ እና ጥርጣሬያቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የኮኮሱን መግለጫ በጸጋ ተቀብለውታል፡፡
መግለጫው እውነትና ፍትህን ታሳቢ አድርጎ አድሏዊ አካሄድን በመቃወም ሃገራቱ ለልዩነቶቻቸው ሰላማዊ እልባትን እንዲሰጡ በሚያስችል መልኩ መውጣቱንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ሚዛናዊ፣ትክክለኛ እና ሁሉንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ስምምነትን ትፈልጋለች ያሉት የቀድሞው ዓለም ባንክ አማካሪ አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር) ኮኮሱ ላሳየው አዎንታዊነት አመስግነዋል፡፡
አሜሪካ ፍጹም የበላይነትን ለመያዝ ለምትታትረው ግብጽ ያሳየችው ወገንተኝነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት እንደማያስችል ይልቁንም እንደሚያጠፋው በአስተያየታቸው አስቀምጠዋል፡፡
የግብጽ ጸብ አጫሪ አካሄድ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ስጋት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ፍላጎቶች ላይ በመረማመድ ለግብጽ ያደረገችው ድጋፍ ደረጃዋን ዝቅ ያደረገ ነውም ብለዋል፡፡
መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ አስተያየታቸውን በኮኮሱ ኦፊሴላው የድረገጽ አድራሻ አስተያየታቸውን ካሰፈሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡
መቶ አለቃ አያልሰው ከአሁን ቀደም በነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታዎች ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡
ለሚዛናዊ መግለጫቸው ህግ አውጪ የምክር ቤት አባላቱን አመስግነዋል፡፡
ለተጀመሩ ድርድሮች መቋረጥ ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ ሳይሆን የግብጽና የአጋፋሪዎቿ ነው ያሉም ሲሆን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ የትኛውም ዓይነት ቀጣናዊ የጸጥታና ደህንነት ችግሮች ኃላፊነቱ የግብጽ እንደሚሆንም ነው ያሰፈሩት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ‘በግብጽ ራስወዳድነት’ ምክንያት ሊደናቀፍ አይገባም እንደ አያልሰው ገለጻ፡፡