ኩባንያው አማዞን፣ ሜታ እና ማይክሮሶፍትን በመከተል ሰራተኞችን በብዛት የቀነሰ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሆኗል
የጎግል እናት ኩባንያ አልፋቤት ገጠመኝ ያለውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ 12 ሺህ ሰራተኞቹን ለመቀነስ መገደዱን ገልጿል።
ከ186 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት አልፋቤት 6 ከመቶውን ነው የቀነሰው።
በ2022 በጎግል ላይ ሰዎች በብዝት የፈለጉት ቃላቶች የትኞቹ ናቸው?
ከ2019 ጀምሮ ኩባንያውን በሃላፊነት የሚመሩት ሱንዳር ፒቻይ፥ ለሰራተኞቹ መቀነስ ውሳኔ ሙሉ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ብለዋል።
የአልፋቤት የሰራተኞች ማህበርም በኩባንያው ውሳኔ ማዘኑን ገልጿል።
በአሜሪካ ከስራ የተሰናበቱት ግለሰቦች በይፋ ደብዳቤ የደረሳቸው ሲሆን፥ የአገልግሎት ክፍያ እና የስድስት ወራት የጤና መድህን ዋስትና ይረጋገጥላቸዋል ነው የተባለው።
ውሳኔው ኩባንያውን ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚታደገው ተገልጿል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ቀዳሚው አልፋቤት፥ ከማይክሮሶፍት የገጠመውን ብርቱ ፉክክር መቋቋም እንደከበደው ሬውተርስ ዘግቧል።
የሰራተኞቹ መሰናበትም ዋነኛ አላማም ወጪውን በመቀነስ ትኩረቱን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ለማድረግ ነው ተብሏል።
የቲክቶክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች መበራከትም የማስታወቂያ ገቢው እንዲቀንስ ማድረጉ ነው የተነገረው።
የአለማችን ሶስተኛው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አልፋቤት፥ ጎግል እና ዩትዩብን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን በስሩ አቅፏል፤ አጠቃላይ ሃብቱም በ2021 359 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ጎግል ብቻ በ2022 ሁለተኛ ሩብ አመት 69 ቢሊየን ዶላር ገቢ አስገኝቷል።
ይሁን እንጂ እናት ኩባንያው አልፋቤት እንደ አማዞን፣ ሜታ እና ማይክሮሶፍት ሁሉ ሰራተኞችን በብዛት በመቀነስ ትርፋማነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ወስኗል።
አራቱ ኩባንያዎች በጠቅላላ የቀነሱት ሰራተኛ ቁጥርም 51 ሺህ ደርሷል።
እስካሁን ሰራተኛ የመቀነስ እቅዱን ይፋ ያላደረገው አይፎን አምራቹ አፕል ኩባንያ ነው።