የኦሮሚያ ክልል ባህልና እሴትን የሚያሳይ ቋሚ የኦንላይን ኤግዚቢሽን በጎግል ላይ ተከፈተ
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ያዘጋጀው “የቱሪዝምና ቴክኖሎጂ” ሳምንት ዛሬ ተከፈተ
በፎቶግራፍና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈው ኤግዚቢሽኑ “በጎግል አርት ኤንድ ካልቸር” ላይ መታየት ጀምሯል
የኦሮሚያ ክልል ባህል እና እሴትን የሚያሳይ ቋሚ የኢንተርኔት (ኦንላይን) ኤግዚቢሽን በጎግል ላይ በይፋ ተከፍቷል።
በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አዘጋጅነት የተሰናዳው ይህ የኢንተርኔት (ኦንላይን) ኤግዚቢሽን “በጎግል አርት ኤንድ ካልቸር” መተግበሪያ ላይ የሚገኝ መሆኑ ተነግሯል።
የኦንላይን ኤግዚቢሽኑ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መካሄድ በጀመረው “የቱሪዝምና ቴክኖሎጂ” ሳምንት ላይ በይፋ የተከፈተ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑንም የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስጀምረውታል።
በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “በጎግል አርት ኤንድ ካልቸር” ላይ 21 የተለያዩ የክልሉን ባህል እና እሴት የሚያሳዩ ይዘቶች መጫናቸውን አስታውቀዋል።
“በጎግል አርት ኤንድ ካልቸር” ላይ የተጫኑት 21 ይዘቶች በክልሉ ባህላዊ መገልገያዎች፣ ምግቦች እና አለባበሶች ላይ ያተኮሩ መሆኑን አቶ ነጋ ወዳጆ አስታውቀዋል።
ሁሉም ይዘቶች “በጎግል አርት ኤንድ ካልቸር” መተግበሪያ ላይ መቀመጡን እና ማንኛውም ሰው መተግበሪያውን በማውረድ፤ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ አሊያም ቪዚት ኦሮሚያ ሲል እነዚህ በምስል እና በጽሁፍ የተደገፉ ይዘቶች ማይት ይችላል ብለዋል።
እነዚህ ይዘቶች በቋሚነት እንደ ዲጂታል ሙዚየም በመተግበሪያው ላይ የሚቀመጡ መሆኑን እና በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ሰው በማንኛውም ሰዓት ከፍቶ ሊመለከት የሚችለው እንደሆነ አቶ ነጋ ለአል ዐይን ገልጸዋል።
በተያያዘ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ያዘጋጀው የቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ሳምንት በዛሬው እለት በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል።