ሩሲያ በጎግል ኩባንያ ላይ የ366 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት አስተላለፈች
ሩሲያ ከዚህ በፊት 98 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል መወሰኗ ይታወሳል
ሩሲያ ውሳኔውን በጎግል ላይ የወሰነችው ከዩክሬን ጋር በተያያዘ ከ 7 ሺህ በላይ ያልተገባ ምስል አሰራጭቷል በሚል ነው
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ያመሩት።
ሩሲያ የአሜሪካዊያን ንብረት በሆነው ጎግል ኩባንያ ላይ 366 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ወስናለች።
በሞስኮ የሚገኘው ታጋንስኪ ግዛት ፍርድ ቤት ጎግል ኩባንያ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ ምስሎችን አሰራጭቷል በሚል የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን አርቲ ዘግቧል።
ዘገባው አክሎም ጎግል ኩባንያ ስለ ዩክሬን ጦርነት ከሰባት ሺህ በላይ ሀሰተኛ ምስሎችን አስራጭቷል ብሏል።
ሩሲያ ሀሰተኛ ምስሎችን ማስተላለፍ በህግ የደነገገች ሲሆን ጎግል ኩባንያ ቅጣቱ የተላለፈበት ሀሰተኛ ምስል በማስተላለፍ እና ያስተላለፋቸውን ምስሎች ከድህረ ገጹ ላይ ለማጥፋት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ሩሲያ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ይሄው ጎግል ኩባንያ ሆን ብሎ ሀሰተኛ ምስሎችን አሰራጭቷል በሚል 98 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ውሳኔ ማስተላለፏ ይታወሳል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎም በሁለቱ ሀገራት እና በተቀረው ዓለም ላይ በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል።
በጦርነቱ ምክንያት በተከሰተው የዋጋ ግሽበት ምክንያትም በበርካታ ሀገራት ኑሮ ተወደደብን በሚል መንግስታት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲደርጉ በሰላማዊ ሰልፍ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
አምስት ወራት የሆነው ይህ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች የምዕራባዊያን ሀገራት ዩክሬንን በጦር መሳሪያ እና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፎችን በመስጠት ላይ ናቸው።