በአደጋው የቆሰሉ ከ40 በላይ ዜጎች ህክምና ላይ ናቸው ተብሏል
በሶማሊያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተለገጸ።አደጋው የተፈጸመው በትናንትናው ዕለት ሲሆን በአሸባሪው አልሻባብ የሽብር ቡድን መፈጸሙን ሮይተርስ የሀገሪቱን የደህንነት ተቋማት ዋቢ አደርጎ ዘግቧል።
በሶማሊያ ከፊል ራስገዝ በምትባለው ጋልሙዱግ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ምክንያትም የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል።
የሽብር ቡድኑ አደጋውን ያደረሰው በመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ሲሆን የአደጋው ሰለባዎች የሽብር ቡድኑን ለመምታት ዘመቻ የጀመሩ የሶማሊያ ወታደሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።
በዚህ አደጋ ምክንያትም 17 ወታደሮች እና 13 ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል።አልሻባብ የሽብር ቡድን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስትን በመጣል በሸሪዓ ህግ የሚመራ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት መታገል ከጀመረ ከ20 ዓመት በላይ አልፎታል።
የሶማሊያ መንግስት በዚህ አደጋ ህይወታቸው እና አካላቸውን ላጡ ሰዎች ማዘኑን ገልጾ በመልሶ ማጥቃት በወሰደው እርምጃ 41 የአልሻባብ ታጣቂዎችን እንደደመሰሰ ገልጿል።
በአደጋው የቆሰሉ ሰዎችን እና ወታደሮችን በአውሮፕላን ወደ መቋዲሾ በማምጣት ህክምና እንደተሰጣቸውም መንግስት አስታውቋል።