የሶማሊያ መሪዎች ምርጫን ለማካሄድ የ “የመጀመሪያ” ውይይት ጀመሩ
በምርጫው መራዘም የተፈጠረው ውዝግቡ ሶማሊያን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል
ምርጫው መች እንደሚካሄድ ግን እስካሁን በመሪዎቹ የተባለ ነገር የለም
የአፍሪካ ቀንዷ ሀገር ሶማሊያ መሪዎች የዘገየውን የሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ያለመ የቅድመ ዝግጅት ውይይት ለማድረግ በሞቃዲሾ ተሰባስበዋል፡፡
በውይይቱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚነስትር፣ አምስቱ የራስ ገዝ ክልሎች መሪዎች እንዲሁም የመዲናዋ ሞቃዲሾ ከንቲባ ተሳታፊ እንደሆኑም ነው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
መሪዎች በመጪው ምርጫ ሊከሰቱ የሚችሉ ውጥረቶችን ለማርግብ በሚቻልበት አጀንዳ ላይ እየመከሩ ነው ተብሏል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ ስብጥር እንዴት መሆን አለበት በሚል ጉዳይም ላይ ነው የሚመክሩት፡፡
መሪዎቹ በምርጫ ዙርያ እየመከሩ ቢሆንም ምርጫው መች እንደሚካሄድ ግን እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡
በየካቲት ወር ያለቀው የፕሬዝዳንት ፎርማጆ የስልጣን ዘመን ለሁለት ዓመታት መራዘሙን ተከትሎ በሶማሊያ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ተከስቶ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ ውጥንቅጥ እንዳያስገባት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ይህም የቀጣናው አሸባሪ ቡዱን አልሸባብ እድሉን በመጠቀም ዳግም አንሰራርቶ የአፍሪካ ቀንድ የደህንነት ሁኔታን ያዳክማል በሚል በርካቶችን አስግቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ፣ በሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት እና በክልል መንግስታት መሪዎች መካከል ስምምነት እንዲፈጠርና የተሻሻለው የምርጫ ሞዴል ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡