ለመልካም ጉርብትና ስትል ግንኙነቱን ዳግም መጀመሯን ሶማሊያ አስታውቃለች
ከኬንያ ጋር አቋርጣው የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም ማስጀመሯን ሶማሊያ አስታወቀች፡፡
ለመልካም ጉርብትና ስትል ግንኙነቱ ዳግም እንዲጀመር ማድረጓን ሶማሊያ አስታውቃለች፡፡
ኬንያ የግንኙነቱን ዳግም መጀመር በጸጋ መቀበሏንም በናይሮቢ የሶማሊያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የሁለቱ ሃገራት መንግስታት ሉዓላዊነትንና ግዛታዊ አንድነትን ባከበረ መልኩ አንዱ በአንዱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ በእኩልነት በጋራ ተጠቃሚነት እና አብሮ መኖር መርሆዎች መሰረት የሁለትዮሽ የወዳጅነት ግንኙነታቸውን ለመጠበቅ ተስማምተዋል፡፡
ሶማሊያ እና ኬንያ በተለያዩ የባህር ድንበር ይገባኛል እና የጣልቃ ገብነት ጉዳዮች ምክንያት ይወዛገባሉ፡፡
ውዝግቡንም ተከትሎ ካሳለፍነው ጥር ጀምሮ ኤምባሲዎቻቸውን ዘግተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል፡፡
ሶማሊያ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው በኬንያ ያሉ የሶማሌ ዲፕሎማቶች በሙሉ በሰባት ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ በማዘዝ ግንኙነቷን ያቋረጠችው፡፡
ለሶማሊያ ውሳኔ ተመሳሳይ የአጸፋ ምላሽ መስጠትን ያልመረጠችው ኬንያ የሻከረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ መደበኛው ለመመለስ የሚረዳ ቡድን እንደምታቋቁም አስታውቃ እንደነበር ይታወሳል፡፡