በቀጣዮቹ 12 ወራት 2 መቶ ሺ ገደማ ሰዎችን ሊገድል እንደሚችልም አንድ ጥናት አመልክቷል
ኮሮና ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ረጅም አመታትን በአፍሪካ ሊቆይ ይችላል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቀጣዮቹ 12 ወራት 190 ሺ ሰዎችን በአፍሪካ ሊገድል እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ፡፡
ድርጅቱ የአህጉሪቱን 47 ሃገራት ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት አስጠናሁ ባለው ጥናት ለወረርሽኙ አፋጣኝ ምላሽ እና ተገቢው ትኩረት ካልተሰጠ ስርጭቱ ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ረጅም አመታትን ሊቆይ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡
ከአሁን ቀደምም እንደ መንግስታት የዝግጁነት እና የምላሽ ሁኔታ ቢለያይም እስከ 10 ሚሊዬን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ አስጠንቅቆ ነበር፡፡
በያዝነው ሳምንት ይፋ የሆነው የድርጅቱ ጥናት የቁጥጥር ስራዎች በታሰበው ልክ ውጤት የማያመጡ ከሆነ ወረርሽኙ በተከሰተበት በዚህ ዓመት ብቻ ከ29 እስከ 44 ሚሊዬን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ፡፡
ይህ ደግሞ በአህጉሪቱ የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ጫናን ሊፈጥር ይችላል እንደ ዘ ጋርዲያን ዘገባ፡፡ በአህጉሪቱ በአንድ ሚሊዬን ህዝብ ዘጠኝ የጽኑ ህሙማን አልጋዎች ብቻ መኖራቸውም ነው የሚነገረው፡፡
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሺዲሶ ሞኤቲ በአፍሪካ ያለው የቫይረሱ ስርጭቱ እንደ ሌሎች የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሃገራት የከፋ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ረጅም አመታትን ሊቆይ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ይህ እንዳይሆን መንግስታት አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡና በስፋት ሊመረምሩ፣ተጠርጣሪዎችን ሊለዩና የታመሙትን ሊያክሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ጥናቱ በድምሩ አንድ ቢሊዬን የሚጠጋ የህዝብ ቁጥር ባላቸው 47 የአህጉሪቱ ሃገራት የተካሄደ ነው፡፡
በአፍሪካ እስካሁን ከ54 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ2 ሺ 74 ሞተዋል፡፡ ቁጥሩ ከባለፉት ሳምንታት ጭማሪ ስለማሳየቱም ተገልጿል፡፡