ሞባይል ስልኮቻችን ኮሮናን መሰል ተህዋሲያን ለማሰራጨት ‘‘የትሮይ ፈረስን ያህል’’ ሚና አላቸው
ሞባይል ስልኮቻችን ኮሮናን መሰል ተህዋሲያን ለማሰራጨት ‘‘የትሮይ ፈረስን ያህል’’ ሚና አላቸው
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በማስተላለፍ ረገድ ብዙውን ጊዜ የምናዘወትራቸው ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻችን (ሞባይል) ድርሻ እንዳላቸው የዱባይ ፖሊስ ኮሚሽን ተመራማሪ ሳይንቲስቶች አስታውቀዋል፡፡
ልብ ሊባል በማይችል መልኩ ቫይረሱን ወደ ቤት በመውሰድና ለሌሎች በማስተላለፍም ረገድ ሞባይል ስልኮች የማይናቅ ድርሻ አላቸው የሚሉት በኮሚሽኑ የፎረንሲክና ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የስነ ህይወትና ዘረ መል (ዲ.ኤን.ኤ) ምርመራ ክፍል ኃላፊ ሜጀር ዶ/ር ራሺድ አል ጋፍሪ ከተለያዩ የአውስትራሊያ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ጥናቶችን አድርገዋል፡፡
ቫይረስን በማስተላለፍ ረገድ ስላላቸው ሚና በተለያዩ ስልኮች ላይ አደረግን ባሉት ጥናትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተህዋሲያንን በስልኮቹ ላይ ስለማግኘታቸውም ነው ገልፍ ኒውስ የዘገበው፡፡
ሞባይል ስልኮች ‘‘የተለያዩ የባክቴሪያ እና ኮሮናን መሰል የቫይረስ ተህዋሲያንን ተሸክመው አግኝተናቸዋል’’ ያሉት ሜጀር ዶ/ር ራሺድ ‘‘ተህዋሲያኑን በማሰራጨት ረገድ ‘የትሮይ ፈረስን ያህል’ ሚና አላቸው’’ ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡
ለዚህም ብዙውን ጊዜ በእጅ መነካካታቸውንና አለመጸዳታቸውን ነው በምክንያትነት ያስቀመጡት፡፡ በአገልግሎት ወቅት ከስልኮቹ የሚወጣው ሙቀት ተህዋሲያኑ ዘለግ ላለ ጊዜ በተለያዩ የስልኩ አካል ክፍሎች ላይ እንዲቆዩ እና እንዲዋለዱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋልም ብለዋል፡፡
ይህ ወደ ቤታችን በምንገባበት ወቅትም ይሁን በትራንስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ላይ ተህዋሲያኑን በቀላሉ እንዲተላለፉ የሚያደርግ ነው፡፡
የወረርሽኙ መተላለፍ ከሃገር ሃገር እየተሸጋገረ ‘ድንበር ዘለል’ ሊሆንም ይችላል፡፡
በመሆኑም የእጅ ስልኮቻችን የወሳኝ መገልገያነታቸውን ያህል ወሳኝ ጥንቃቄንም ይሻሉ፡፡ ዘወትር መጽዳትንም ይፈልጋሉ፡፡
ሰባ በመቶ የአልኮልነት ይዘት ባላቸው ሳኒታይዘርን መሰል ማጽጃዎች በመጠቀም ሳያመነቱ ማጽዳትም የግድ ነው እንደ ተመራማሪው ገለጻ፡፡