አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፣ አምባሳደር ታየን በመተካት በተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ ይሆናሉ
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው መሾማየውን የዲኘሎማሲ ምንጮች ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን እና ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱን ተከትሎ ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ የዲፕሎማሲ ጫናዎች እየቀለሉ መጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፈረንጆቹ አዲሱ 2023 ዓመት ከመግባቱ በፊት ዲፕሎማቶቿን ወደ አዲስ አበባ ጠርታ ለአዲስ እና ነባር ተልዕኮዎች ስልጠና ስትሰጥ ቆይታለች፡፡
ከስልጠናው ጎን ለጎንም ከዚህ በፊት በተለያዩ ሀገራት ተመድበው ሲሰሩ ለነበሩ አምባሳደሮች የተመሰገኑ ሲሆን በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳዳር ታዬ አጽቀስላሴ፣ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከቀናት በፊት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴዔታ ሀላፊነታቸው የተነሱት እና በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴን ተክተው መሾማቸውን ምንጮች ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ እና ለንደን ሳወዝ ባንክ ሁለተኛ ድግሪያቸውን የያዙት አምባሳደር ተስፋዬ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከሰሞኑ ከግብርና ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ኡመር ሁሴን ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተደርገው ተሾመዋል ብለዋል ምንጮች፡፡
እንዲሁም ላለፉት አመታት በተመድ ኒዮርክ እና ስዊዘርላንድ ጀኔቭ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ የነበሩት አምባሳደር ማህሌት ሀይሉ ደግሞ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል።
አዲስ የተሸሙት አምባሳደሮችም በነገው ዕለት በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ስምሪት እንደሚገቡ ከምንጮቻችን አረጋግጠናል፡፡