በተመድ እና በሌሎች መድረኮች ኢትዮጵያዊያን “የሰለጠኑ አይደሉም፤ ስሜታዊ ናቸው ብለውናል” - አምባሳደር ታየ
ያለፉት ሁለት አመታት በዲፕሎማሲ ለኢትዮጵያ ከባድ አመታት ነበሩ ብለዋል አምባሳደር ታየ
ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ቋሚ አባል እንድትሆን ፍላጎት እንዳላት አምባሳደር ታየ ገልጸዋል
አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ ናቸው፡፡ አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ በጦርነት እና ከዚያ ቀደም ሲል በህዳሴው ግድብ ጉዳይ በተመድ ስሟ እየተነሳ አጀንዳ ስትሆን ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከኒው ዮርክ ወደ ኢዲስ አበባ ከመጡት አምባሳደር ታዩ አጽቀስላሴ ጋር ስላለፉት ሁለት ዓመታት የተመድ ቆይታቸው፣ ስለ ተመድ ማሻሻያ፣ስለየዲፕሎማሲ ጫናዎች እና ሌሎችም ጉዳዮች ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን አቅርበነዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት ለደረሰባት የዲፕሎማሲ ጫና ጦርነቱ ትልቁ ምክንያት ሊሆን ቢችልም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን?
አምባሳደር ታዬ፡-ያለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ ዓመታት ነበሩ፣ የነበርንበት ጦረነት መዳረሻ እና የመጨረሻው ግብ ምን እንደሆነ ያለየለት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ተማርን በሚሉ ልጆቿ የተፈተነችበት ጊዜም ነበር፤ከዚህ በፊት የነበረው ትውልድ የነበረበትን ቅራኔ መፍታት ሳይችል በመቅረቱ ችግሩ ሲንከባለል ሲንከባለል ቆይቶ በአሁኑ ትውልድ ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡ ይህ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የፖለቲካ ሂደት ባህሉ ትክክል ስላልነበረ ወደ ጦርነት አመራ፡፡ የውስጥ ችግራችንን በሰለማዊ መንገድ መፍታት ሳንችል ወደ ጦርነት መግባታችን ሲፈልጉን ለነበሩ ጠላቶቻችን ተመችቷቸው ነበር፡፡ ጥቅማችን በባሩድ ይመለሳል ብሎ የሚያስብ ሰው መኖሩ ወደ ጦርነት አምርተናል፡፡ በዚህ ጦርነት ያልታዩ ብዙ ቁስሎች አሉ፡፡ ያልታከሙ ብዙ ህመሞች አሉ፡፡ እነዚህ ህመሞቻችንን በማሰብ ምንም ልናመጣ አንችልም፡፡ የፖለቲካ ትዕግስት አልነበረንም፡፡ ይህ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ትንሹ ነገር የተረከብነውን ማስቀጠል ነው፡፡ ሰላም የጀግኖች ጦርነት ደግሞ የጅሎች ድርጊት ነው፡፡ ዓለም እንዲያከብረን እና በዓለም መድረክ እንዳንቀል ከተፈለገ በማንኛውም መንገድ ሰላምን ማስቀጠል እና በመነጋገር ችግር እንደምንፈታ ማሳየት አለብን፡፡ በተመድ እና በሌሎች የአደባባይ መድረኮች ላይ ብዙዎች ኢትዮጵያዊያን አቅም የላቸውም፣ የሰለጠኑ አይደሉም ስሜታዊ ናቸው ብለውናል፡፡ አትችሉም ሲሉን ኢትዮጵያን በፖለቲካ መነጽር ብቻ አትመልከቱ እኛ ባህል፣ ታሪክ እና ማንነት ያለን ሰፊ ህዝቦች ነን ስንል ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ የሰላም ስምምነት ፈርመን ለተግባራዊነቱ መስራት ጀምረናል፡፡ ይሄን ቀጥለን በዓለም መድረክ ቀና ብለን መሄዳችንን እንቀጥላለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የ2023 የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
አምባሳደር ታዬ፡-ልዩነቶች ቢኖሩንም ሀገርን የሚበትኑ ጉዳዮች ሊሆኑ አይገቡም፡፡ፈተናዎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ድህነት አለብን፡፡ የድህነታችን ስፋት ባህሪያችንን አጥፍቶታል ብዬ አልወስድም፡፡እንደ ሀገር የፖለቲካ ባህላችንን ማስተካከል አለብን፤ እንደህዝብ መቀጠል አለብን፡፡ሌላኛው ፈተናችን ልዩነቶችን በጀግንነት በሰለጠነ መንገድ መፍታት መልመድ አለብን፡፡ በሰይፍ ችግሮቻችንን ለመፍታት መሞከር ማቆም አለብን፡፡ ብዙ ሀገራት ጽንፈኝነትን ወደ ዳር ገፍተው ወስደዋል፡፡ እኛም ጽንፈኝነት ወደ ማዕከል እንዳይመጣ ማድረግ አለብን፡፡ በዓለም መድረክ መጉላት የምንችለው የውስጥ ጉዳዮቻቸችንን ስንፈታ ብቻ ነው፡፡ ድሃ ብንሆንም ረጅም ዓመት እና ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ሰላም በመጀመራችን ድሮ የናቁን ሀገራት ለካ ይችላሉ እያሉን ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ችግር ሊገጥመው ይችላል እኛም ከችግር መውጣት እንችላለን፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ተራ እና መናኛ ሀገር አይደለችም፣ ብዙ ሀገራት ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥሟቸው ያውቃል፡፡ የመንግስት መኮስመን እና የመንግስታት መፍረስ አደጋ በየትኛውም ሀገር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እኛም ከችግራችን መውጣት እንችላለን፣ ውስጣዊ የፖለቲካ ፈተናዎቻችንን እናልፋቸዋለን፡፡እጅግ ብዙ ሀገራዊ፣ አካባቢያዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ቢኖሩም እኛ የሀገር ውስጥ ጉዳዮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከቻልን ሌላው ሁሉ ይቀላል፡፡ የ2023 ዓመት ዋነኛ ስራችን እና ፈተናችንም ከዚህ አንጻር በምንሰራው ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ተመድ የኢትዮጵያ ዋነኛ የዲፕሎማሲ እና ፖለቲካ ጫና መፍጠሪያ ማዕከል የሆነው ለምን ነበር?
አምባሳደር ታዬ፡- ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት መስራች ሀገር ናት፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ በአስር ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ብዛት ካላቸው ሀገራት እስከ በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያላቸው ሀገራት እኩል ወንበር አላቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ተመድ እና በስሩ ያሉ ብዙ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ አይነቱ ብዙ ተፅዕኖዎችን ሲፈጥሩብን ነበር፡፡ በተለይም የበለጸጉ ሀገራት ተቋማቱ የሚንቀሳቀስባቸው በጀቶች ከእኔ ህዝብ ግብር ከፋዮች የሚመጣ ነው እና እኔ የምለውን አድርግ የሚሉ ሀገራት ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ቀላል የማይባሉ የተመድ ተቋማት እና አመራሮች መርህን ተከትለው ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሲያደርጉም ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት እና መሪዎች ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረጋቸውም ጥርስ የተነከሰባቸው እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ብዙ ሀገራት በተናበበ መንገድ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን እንደ አንድ ርዕስ አድርጎ እንዲወያይ፣ ሁሌ አጀንዳ እንድንሆን በተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያላትን ታሪክ፣ ብርታት እና ሌሎች ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ባስገቡ እንደ ህንድ፣ ጃማይካ እና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ትብብር እንዲሁም ብዙዎች ስላገዙን ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡-ብዙ ሀገራት በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ በዚህ መድረክ ላይ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የተጀመረ ጥረት ይኖር ይሆን?
አምባሳደር ታዬ፡- ብዙ የዓለማችን ሀገራት ተመድ እንዲሻሻል በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው ሀገራት ብዛት እንዲሻሻል የሚጠይቁ አሉ፡፡ ለምሳሌ ቡድን አራት ወይም ጂ4 የሚባለው ቡድን ስብስብ ህንድ፣ ጀርመን፣ ብራዚል እና ጃፓን ካላቸው ኢኮኖሚ፣ የህዝብ ብዛት እና ሌሎች ሁኔታዎች አንጻር የጸጥታው ምክር ቤት አባል መሆን አለብን ብለው እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም ተመድ እንዲሻሻል ከሚፈልጉ እና ከጠየቁ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ አሁን ያለው ተመድ የተቋቋመው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የነበሩ የጦርነት ሁኔታዎችን ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመው ነው፡፡ አሁን ደግሞ ዓለማችን ያለችበት ሁኔታ ያኔ ከነበረው ጋር የተለየ ነው፡፡ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በይፋ የሚስማሙበት ነገር ቢኖር የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ቁጥር እንዳይጨመር ነው፡፡የአፍሪካ ህብረትም በይፋ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ እና አምስት ተለዋጭ መቀመጫዎች እንዲኖሯት ጠይቋል፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ህብረትን አቋም ትደግፋለች፡፡ በዚህ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ቋሚ አባል እንድትሆን ፍላጎት አለን፣ ትልቅ ህዝብ እና ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ይሁንና በዚህ ጉዳይ በአፍሪካ የተለያዩ ውይይቶች በተለያዩ መድረኮች ይካሄዳሉ፡፡ እኛ ግን በአፍሪካ ህብረት ስር በሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች ላይ የሚወሰነውን እንቀበላለን፡፡