አሜሪካና አጋሮቿ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ከቻይናና ሩሲያ ጋር ተፋጠጡ
አሜሪካ፤ ቻይና እና ሩሲያ ሰሜን ኮሪያን እያባበሉ ነው በሚል ወቅሳለች
ቻይናና ሩሲያ ለኮሪያ ሰርጥ ውጥረት ተጠያቂው አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ የምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ ነው ብለዋል
ዩናይትድ ስቴትና አጋሮቿ በሰሞነኛ የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ማስወንጨፍ ምክንያት ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ተፋጠዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ እንደተናገሩት የሰሜን ኮሪያ እርምጃ የወታደራዊ ጡንቻዋን ለማሳይት ሳይሆን ጎረቤቶቿን በፍርሃት ለማሸበር ነው።
አምባሳደር ግሪንፊልድ ፒዮንግያንግ 59 የባሊስቲክ ሚሳይል በዚህ ዓመት ብቻ አስወንጨፋለች በማለት ለነጥባቸው ማሳያ አቅርበዋል።
- አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የኒውክር ሙከራ የማስቆም አቅም ያላቸው ሩሲያ እና ቻይና ናቸው አለች
- ሰሜን ኮሪያ፤ አሜሪካ ትንኮሳዋን የማታቆም ከሆነ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ አስጠነቀቀች
ከእነዚህም 13ቱ ከጥቅምት ወር መገባደጃ ጀምሮ የተወነጨፉ ናቸው ያሉ ሲሆን፤ በደቡብ ኮሪያ የባህር ዳርቻ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ተፅዕኖ ያሳረፈውን ጨምሮ በዚህ ዓመት የፒዮንግያንግ ጦርነት ከመግጠም በላይ እርምጃ ወስዳለች ማለታቸውን ኤቢሲ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያ ይህ እንቅስቀሴ የውትድርና አቅሟን ከማሳየት የዘለለ ነውም ብለዋል። ይልቁንም በቀጠናው ውጥረቶችን ለመጨመር እና በጎረቤቶች መካከል ፍርሃት ለመፍጠር በመፈልግ ነው ብለዋል።
አምባሳደሯ ከ15ቱ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት 13ቱ የሰሜን ኮሪያን ተግባር ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ አውግዘዋል ብለዋል ።
ነገር ግን ፒዮንግያንግ በሩሲያ እና በቻይና ተጠብቃ ቆይታለች ሲሉም ጣታቸውን የቀሰሩት ግሪንፊልድ፤ ሁለቱ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣላቸውን ማዕቀቦች ችላ ብለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ግሪንፊልድ ሀገራቱ ሰሜን ኮሪያ በእንቅስቀሴዋ እንድትገፋ አበረታተዋል በማለት “ምክር ቤትቱን መሳለቂያ አድርገዋል’’ብለዋል ።
የቻይናው የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር ዣንግ ጁን የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፍ ከአምስት ዓመት እረፍት በኋላ ዳግም የተመለሰው የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖች ጋር ከመጀመሩ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው ሲሉ ውንጀላውን ተቃውመዋል።
የሩስያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል አምባሳደር አና ኢቭስቲኒቫ በበኩላቸውም በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ለደረሰው የከፋ ሁኔታ አሜሪካ ተጠያቂ ናት ሲሉ መልሰዋል። ለውጥረቱ “ዋሽንግተን የፒዮንግያንግን ማዕቀብ በመጠቀም እና ጫና በመፍጠር በአንድ ወገን ትጥቅ እንድትፈታ የማስገደድ ፍላጎት” ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ከሳምንት በፊት የጀመረው የዩናይትድ ስቴት እና የደቡብ ኮሪያ ልምምድን ግዙፍነት በመጥቀስ፤ ልምምዱ 240 የሚጠጉ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ያካተተ ነው ብለዋል። እናም ልምምዱ በዋናነት በሰሜን ኮሪያ ግዛት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለማድረስ ነው" ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።
የቻይናና ሩሲያ ምላሽ ግን ለአሜሪካ አልተዋጠላትም። “ይህ የሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳ እንጂ እውነተኛ ምክንያት አይደለም” ሲሉ አምባሳደር ግሪንፊልድ መልሰዋል።
ለረጅም ጊዜ የቆየው ወታደራዊ ልምምድ “እንኳንስ ለሰሜን ኮሪያ ይቅርና ለማንም ስጋት አይፈጥርም” በማለትም አክለዋል።