አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ጀመሩ
አምባሳደሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል አሳስበዋል
ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ጋር ጋር እየተወያዩ የሚገኙት ፌልትማን በቀጣይ ከ ጠ/ሚ ዐቢይ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል
ከሰሞኑ በካይሮ ፣ አስመራ እና ካርቱም ጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል፡፡
ዲፕሎማቱ ከሰሞኑ ከግብፅ ፣ ከኤርትራ እና ከሱዳን መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያም ይፋዊ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል፡፡ አምባሳደር ፊልትማን ዛሬ ከኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር ውይይት እያደረጉ ነው፡፡
ሚኒስትሩ እና ዲፕሎማቱ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በኩል የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ተገኝተዋል ሲል ፋና ዘግቧል፡፡
አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎችም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
በጆ ባይደን አስተዳደር በቅርቡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሸሙት አምባሳደር ፌልትማን በቀጣናው ያሉ አለመግባባቶች ፣ በተለይም የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ በሀገራቸው ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
አምባሳደሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ሦስቱም ተደራዳሪ ሀገራት ካልፈቀዱ በስተቀር አሜሪካ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡