"ሱዳን የግድቡን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ስለወሰደች ብቻ የሚወሰን ነገር የለም"- ኢ/ር ጌዲዮን አስፋው
ሱዳን ከሰሞኑ የግድቡን ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው
ግድቡ ሃገራቱ በተስማሙበት የሙሌት ሰንጠረዥ መሰረት የሚፈጸም መሆኑንም ተዳራዳሪው ገልጸዋል
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት የሚፈጸመው ሶስቱም ሃገራት በተስማሙባቸው መርሆች መሰረት መሆኑን የግድቡ ቴክኒክ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ተናገሩ፡፡
ኢንጂነር ጌዲዮን የግድቡ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢም ናቸው፡፡
የግድቡን ሙሌት አስመልክተው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሰብሳቢው ሙሌቱ የሦስቱ ሀገር ተወካይ ባለሙያዎች በሠሩት የሙሌት ሰንጠረዥ መሰረት የሚፈጸም መሆኑን ገልጸዋል።
የሙሌት ሰንጠረዡ አምስት አምስት ሆነው ከእያንዳንዱ ሃገር በተውጣጡ 15 ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው፡፡
ባለሙያዎቹ እ.ኤ.አ በ2018 ተስብስበው በነበሩት የሀገራቱ የውሃ፣ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ሚኒስትሮች የተወከሉ ናቸው፡፡
ባለሙያዎቹ በዝርዝር ተወያይተው ባቀረቡት የተሟላ ሃሳብ መሰረት ረቂቅ የሙሌት ሰንጠረዡ ተዘጋጅቷል፡፡
በሰንጠረዡ መሰረትም ግድቡ “በሀምሌ እና ነሐሴ ወራት እንዲሁም ዝናቡ ቀጣይነት ካለው በወርሃ መስከረምምሊሞላ ይችላል” እንደ ኢንጂነር ጌዲዮን ገለጻ።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በዚሁ መሰረት ነው የተከናወነው፡፡ ሁለተኛው ዙር ሙሌትም በእንዲሁ ዐይነት መንገድ የሚፈጸም ይሆናል።
ሙሌቱ ይጎዳናል የሚል ነገር ሊነሳ የሚገባም እንዳይደለም ነው ኢንጂነር ጌዲዮን የተናገሩት፡፡
“ኢትዮጵያ ሙሌቱን በተመለከተ ቀደም ብላ ያሳወቀችው ጉዳይ በመሆኑ ከዚያም በላይ በሦስቱ ሀገራት ስምምነት የተደረገ በመሆኑ ለወደፊት በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ” እንደማያመጣም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የግድቡ አሞላል ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ የሚያስችል ግብዣ ማቅረቧን የጠቆሙት ተደራዳሪው “በሱዳንና በግብጽ በኩል ቅን አስተሳሰብ ቢኖር የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ስምምነት መፈራረም ይቻል ነበር” ብለዋል።
ጉዳዩ በቀጣይ ውይይቶች ዳግም ይታያል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ሱዳን ከሰሞኑ የግድቡን ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምትወስደው አስታውቃለች፡፡
ይህን በተመለከተ የተጠየቁት ኢንጂነሩ “ሀገራት የሚመስላቸውንና የሚያዋጣቸውን ዕርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ” ብለዋል ሱዳንም “ያዋጣኛል ብላ ካሰበች” መሄድ እንደምትችል በመጠቆም፡፡
ሆኖም “አንዱ ስላቀረበ ብቻ ዝም ተብሎ የሚወሰን ጉዳይ እንደሌለ” ማወቁ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል፡፡
የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡
ለዚህም ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን የግድቡ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውን የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡