በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የሚካሔደው የሕዳሴ ግድብ ድርድር መቀጠል እንዳለበት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መልዕክተኛ ገለጹ
የዲአር ኮንጎ ፕሬዝደንት እና የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ቺሲኬዲ ለስራ ጉብኝት ካርቱም ገብተዋል
የሕዳሴው ግድብ ልዩነት በድርድር መፈታት እንዳለበት ሱዳን እንደምታምን አል-ቡርሃን ገልጸዋል
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሌተናንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ጋር በካርቱም ተወያይተዋል።
የአሜሪካ መልዕክተኛው ፊልትማን በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ታዛቢነት የሚካሔደው የሕዳሴ ግድብ ድርድር መቀጠል እንዳለበት በአፅንዖት ገልጸዋል፡፡
አል-ቡርሃን በበኩላቸው የዓባይ ውሃ ምንጭ በሆነችው ኢትዮጵያ እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች መካከል ያለው ልዩነት በድርድር መፈታት እንዳለበት ሱዳን እንደምታምን ገልጸዋል፡፡ የአልቡርሃን ንግግር ሀገራቸው ወደ አፍሪካ ሕብረት መራሹ ድርድር ልትመለስ እንደምትችል አመላካች ነው፡፡ በሦስቱ ሀገራት መካከል ትብብር እንደሚያስፈልግም ነው አል ቡርሃን የተናገሩት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት እና የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ አንቶይን ቺሲኬዲ ለአንድ ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ሱዳን ገብተዋል ፡፡ ፕሬዝደንቱ ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሉዓላዊነት ሌተናንት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን አቀባበል አድርገውላቸዋል ፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ፣ በአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፌሊክስ ቺሲኬዲ ሰብሳቢነት ከአንድ ወር በፊት በኪንሻሳ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ከዚህ ካልተሳካው ውይይት በኋላ ግብፅ እና ሱዳን የሕዳሴው ግድብ ድርድር ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ አለበት፤ አ ሜሪካ እና አውሮፓ ጣልቃ ይግቡ እና ሌሎች የተለያዩ ሀሳቦችን ሲያነሱ ቆይተዋል።
ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ጉዳይ አሳሪ ስምምነት ሳይፈጸም ኢትዮጵያ ሁተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን የለባትም በማለት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ደግሞ የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ስር መቀጠል አለበት የሚል አቋሟን ስታንጸባርቅ መቆየቷ ይታወሳል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፊታችን ነሐሴ ወር 700 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚካሄድ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አስታውቃለች።