ባራክ ኦባማ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሁለተኛው ተወዳጅ መሪ ነበሩ ተባለ
አሜሪካ በታሪኳ እስካሁን 46 ፕሬዝዳንቶች ተፈራርቀው የመሯት ሲሆን ሲ-ስፓን የተሰኘው የጥናት ተቋም የሐገሪቱን ፕሬዝዳንቶች ተቀባይነት እና የመሪነት ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ተቋም ሪፖርት መሰረት አብርሃም ሊንከን ምርጡ ፕሬዝዳንት የተሰኙ ሲሆን ባራክ ኦባማ፣ ሮናልድ ሬገን ከምርጦቹ ፕሬዝዳንቶች መካከል መጠቀሳቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በፕሬዝደንት ባይደን የተተኩት አወዛጋቢው እና 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ መካከለኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
እንደ ጥናቱ ከሆነ ምርጥ አምስት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች አብርሃም ሊንከን፣ ጆርጅ ዋሸንግተን፣ፍራንክሊን ሩዝቬልት፣ቲዮዶር ሩዝቬልት፣ እና ዲዋይት አይዘናወር ናቸው ተብሏል፡፡
በመካከለኛ ደረጃ ደግሞ ሄነሪ ሀሪሰን፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ ፍራንክሊን ፒርስ፣ አንድሪው ጆንሰን እና ጀምስ ቡቻነን ተጠቅሰዋል፡፡
አሜሪካን ከእርስ በርስ ጦርነት እንደታደጉ የሚናገርላቸው አብርሃም ሊንከን ሀገሪቱን ከመበታተን በማዳን ባለውለታ ፕሬዝዳንት የተባሉ ሲሆን የመጀመሪያው የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሸንግተን ደግሞ ሀገሪቱ በዲሞክራሲ እንድትመራ ፈር የቀደዱ መሪ ተብለው ተመርጠዋል፡፡
ፍራንክሊን ሩዝቬልት ደግሞ አሜሪካ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በድል እንድትወጣ ትልቅ የአመራር ጥበብ ማበርከታቸው ሲገለጽ የኮሪያ ጦርነት እንዲያበቃ ውሳኔ ያሳለፉት ፕሬዝዳንት አይዘናወር ሌላኛው የአሜሪካ ባለውለታ ፕሬዝዳንት ናቸው ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቶቹ በዋናነት የተመዘኑት ለአሜሪካ የነበራቸው ራዕይ ምን ነበር የሚለው ዋና መመዘኛ ሲሆን በአስቸጋሪ የአሜሪካ እና የዓለም ፈተናዎች ዙሪያ ፕሬዝዳንቶቹ ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች ሌላኛው መመዘኛ ነው፡፡
በዚህ ጥናት ላይ በአሜሪካ ታዋቂ ዩንቨርሲቲዎች ያሉ ምሁራን አስተያየት የተካተተ ሲሆን ፕሬዝዳንት ቢል ክልንተን በአሜሪካ ፕሬዝዳናት ታሪክ ፈተና ያልገጠመው መሪ የተባለ ሲሆን ጀምስ ቡቻነን የከፋው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ቡቻነን በስልጣን ጊዜያቸው ወቅት በባሪያ ንግድ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ እየቻሉ ባለመወሰናቸው አጋጣሚው ከእጃቸው እንደወጣ እና ደካማው መሪ በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም አሌክሳንደር ትሩማን ሌላኛው ደካማው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የተባሉ ሲሆን አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ የስልጣን ጊዜያቸው ያላለቀ በመሆኑ ደረጃ አልወጣላቸውም ተብሏል፡፡