ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው በ ‘ኤሌክቶራል ኮሌጅ’ ተረጋገጠ
ባይደን በአውሮፓውያኑ ጥር 20 ቃለ መሓላ ፈጽመው ስልጣናቸውን ይረከባሉ
“የሕግ የበላይነት ፣ ህገ-መንግስታችን እና የህዝብ ፍላጎት አሸንፈዋል” ጆ ባይደን
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተካሔደ በኋላ በየግዛቱ በጥቂት ተወካዮች በሚካሔደው የውክልና ድምጽ ምርጫ ከ538 የውክልና ድምጾች 306 ድምጽ በማግኘት ጆ ባይደን ትናንት ምሽት በይፋ 46ኛ ፕሬዝዳንትነታቸው ተረጋግጧል፡፡
‘ኤሌክቶራል ኮሌጅ’ የሚል ስያሜን በያዙት በእነዚህ የውክልና መራጮች ከሚሰጠው ድምጽ ውስጥ 270 እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን ማግኘት ለአሸናፊነት የሚያበቃ ሲሆን ባይደን በዋናው ምርጫ ያገኙትን ያክል 306 ድምጽ አግኝተዋል፡፡
‘ኤሌክቶራል ኮሌጁ’ ማሸነፋቸውን ካረጋገጠላቸው በኋላ ጆ ባይደን ባደረጉት ንግግር “የሕግ የበላይነት ፣ ህገ-መንግስታችን እና የህዝብ ፍላጎት አሸንፈዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"የዴሞክራሲ ነበልባል በዚህች ሀገር ከረዥም ጊዜ በፊት በርቷል፡፡ እናም አሁን ምንም አይነት ነገር ፣ ወረርሽኝ ወይም በስልጣን መመካት ይህን የዴሞክራሲ ነበልባል ሊያጠፋው እንደማይችል አውቀናል" በማለትም ትራምፕን ወርፈዋል፡፡
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ጥራምፕ ያቀረቡትን ክስ ውድቅ ማድረጉንም ባይደን አድንቀዋል፡፡
በ ‘ኤሌክቶራል ኮሌጅ’ የውክልና ድምጽ የሚሰጠው በሀገሪቱ ህግ መሰረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታሕሣሥ በገባ ከሁለተኛው ረቡዕ በኋላ በሚውለው የመጀመሪያ ሰኞ እለት ሲሆን ይህም ዋናው ምርጫ ከተካሔደ በኋላ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ግዛቶች በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው በማሰብ ነው፡፡
የየግዛቱ አስተዳዳሪዎች ፣ የፓርቲ ታዋቂ ሰዎች አሊያም የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው ምርጫውን የሚያደርጉት፡፡ ይህ በጥቂት ሰዎች የሚካሔደው የውክልና ምርጫ በአሜሪካ የተለመደ ቢሆንም ለውጥ ያመጣል ተብሎ ስለማይታሰብ እስካሁን ትኩረት አይሰጠውም፡፡ አሁን ላይ ግን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሽንፈታቸውን አለመቀበላቸው ሁለተኛው ምርጫ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡
ምንም እንኳን አሁንም ድረስ ትራምፕ መሸነፋቸው ባይዋጥላቸውም ፣ ጆ ባይደን በአውሮፓውያኑ ጥር 20 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ስልጣናቸውን ይረከባሉ፡፡
ምንጭ፡ ሲኤንኤን