ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ይፈልጋሉ
የኮትዲቮር ፕሬዘዳንት አላሳን ኦታራ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያን እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡
የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዘዳንቱ የማሻሻያ ሃሳቡን በቀጣዮቹ 4 ወራት ለሃገሪቱ ፓርላማ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ አባባል ከሆነ ሃሳቡ ህገመንግስቱን ወጥነት ያለውና ይበልጥ የዳበረ ያደርገዋል፡፡
ሆኖም ሃሳቡ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መገባደጃ ላይ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ተቀናቃኝ ሆነው እንደሚፎካከሩ ያስታወቁትን የቀድሞዎቹን የሃገሪቱን ፕሬዘዳንቶች የ74 ዓመቱን ሎረን ባግቦን እና የ87 ዓመቱን ሄንሪ ኮናን በዴን ከምርጫው ገለል ለማድረግ ነው በሚል ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡
የ78 ዓመቱ አላሳን ግን ምንም እንኳን ሃሳቡን በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ባይሰጡም እንዲህ ዓይነት ዓላማ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
እንዲያውም የዕድሜ ገደብን ማስቀመጡ ራሳቸውንም ከፉክክሩ ውጭ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በመግለጽ እንደማያደርጉትና ማንኛውም ፍላጎቱና ዝግጁነቱ ያለው አካል መሳተፍ እንደሚችል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አላሳን የሎረን ባግቦን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ለረጅም ዓመታት ከዘለቀውና የ3 ሺ ዜጎችን ህይወት ከነጠቀው የርስበርስ ግጭት በኋላ ነው እ.ኤ.አ በ2011 መንበረ ፕሬዘዳንትነቱን የተቆናጠጡት፡፡
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2016 የተደረገው ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ፕሬዝዳንቱ በምርጫ በድጋሚ ሊወዳደሩ የሚችሉበትን እድል ሰጥቷቸዋል፡፡