ጃፓናዊቷ ኬን ታናካ በ117 ዓመት ዕድሜያቸው የዓለምን ሪከርድ ይመራሉ
117ኛ የልደት በዓላቸውን በደቡባዊ ጃፓን ፉኮካ ያከበሩት ኬን ታናካ አሁንም የዓለምን የአዛውንቶች መዝገብ በቀዳሚነት ይመራሉ፡፡
116ኛ የልደት በዓላቸውን ባለፈው ዓመት ወርሃ የካቲት መጨረሻ ላይ ያከበሩት ታናካ በወቅቱ በ116 ዓመት ከ66 ቀናቸው በህይወት ያሉ ቀዳሚዋ አዛውንት በሚል በጊነስ የዓለም ሪከርዶች መዝገብ ላይ ሰፍረዋል፡፡ አሁን ደግሞ 117 ዓመታቸውን ደፍነው የራሳቸውን ሪከርድ ሰብረዋል፡፡
ይህ የታናካ ሪከርድ በዕድሜ የገፉ ጃፓናውያን ቁጥር እየተበራከተ ለመምጣቱ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ሆኖም ግን የውልደት መጠኑ እጅግ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ በሀገሪቱ ቀጣይ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖረው በሚል ስጋት አሳድሯል፡፡
በጃፓን የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር ባለፈው ዓመት በ5 ነጥብ 9 በመቶ ቀንሷል፡፡ በዓመቱ 864 ሺ ህጻናት ብቻ ናቸው የተወለዱት፡፡
ይህም የሀገሪቱ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ መረጃዎችን ማሰባሰብ ከጀመረበት እኤአ ከ1899 ወዲህ ዝቅተኛው ነው ተብሏል፡፡
የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ-ጊነስ ቡክን መረጃ ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ እኤአ በ1903 የተወለዱት ታናካ የ4 ልጆች እናት ናቸው፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ