ቴህራን በዋሺንግተን ላይ ጥቃት ከሰነዘረች አሜሪካ 52 የተመረጡ የኢራን ስፍራዎችን ለማጥቃት መዘጋጀቷን ገለጸች፡፡
ወትሮውንም ዐይንና ናጫ የሆኑት አሜሪካና ኢራን፣ አሁን ላይ ግንኙነታቸው ይበልጥ ሻክሮ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ሆነዋል፡፡
ከኢራን የኒዩክሌር ማብላላት እና የሽብርተኝነት ፍረጃ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ተደራራቢ ማዕቀቦችን በጫንቃዋ ላይ ተሸክማ ረዥም አመታትን ተጉዛለች፡፡
በኦባማ የመጨረሻ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ሁለቱ ሀገራት የተሻለ መግባባት ፈጥረው የገላጋዮቻቸውን አንተም ተው አንቺም ተይ ተማጽኖ በመስማት ሰላምን ወደማውረድ ቢንደረደሩም፣ የትራምፕ ወደ ዙፋን መምጣት የሰላም ተስፋዎችን ሁሉ መና አስቀርቷል፡፡
በዘመነ ኦባማ የተደረሰው ስምምነት የአሜሪካን ጥቅም የሚጎዳ ነው ያሉት ፐሬዝዳንት ትራምፕ፣ ስምምነቱን ቀደው ጥለውታል፡፡
በዚህም ወደ ቀድሞ ጽንፉ የተመለሰው የቴህራንና ዋሺንግተን ግንኙነት እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑት የኢራን የጦር መሪ ቃሲም ሶሌይማኒ በአሜሪካ ጥቃት መገደል ጋር ተያይዞ አሁን ይበልጥ ተካርሯል፡፡
የጦር መሪዋን መገደል ተከትሎ ኢራን በአሜሪካ ላይ ጠንካራ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ደጋግማ አስታውቃለች፡፡
ይህ የኢራን ዛቻ ያላማራቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ፣ ቴህራን በአሜሪካ ንብረትና ይዞታዎች ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር አበክራ እየገለጸች መሆኑን በመጥቀስ፣ የአሜሪካ አጸፋ ደግሞ እጅግ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡
ኢራን የጦር መሪዋን መገደል ተከትሎ በአሜሪካ ላይ ምንም አይነት ጥቃት ከፈጸመች አሜሪካ ለጥቃት 52 የኢራን የተለያዩ ስፍራዎችን ለይታለችም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፡፡ ከነዚህም አንዳንዱ ለኢራን እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ስፍራዎች ሲሆኑ ባህላዊ እሴታቸውም ወደር የሌለው መሆኑን በጽሁፋቸው አካተዋል፡፡ እናም ቴህራን በዛቻዋ ገፍታበት አሜሪካን ከተነኮሰች፣ መንግስታቸው በነዚህ የኢራን ወሳኝ ሰፍራዎች ላይ ፈጣንና ከባድ አጸፋዊ ጥቃት ትሰነዝራለች ብለዋል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፡፡
አሜሪካ የመረጠቻቸው 52 የኢራን ኢላማዎች፣ እ.ኤ.አ ከ1979 መጨረሻዎች ጀምሮ ኢራን ከአንድ ዓመት በላይ አግታ ያቆየቻቸውን 52 አሜሪካዊያን የሚያመለክቱ ተምሳሌቶች ናቸው አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት እንዳሉት፡፡
የፕሬዝዳንቱን የትዊተር መልዕክት ተከትሎ አንድ የአሜሪካ መንግስት ተቋም መረጃ በኢራናውያን ከመጠለፉ ውጭ ኢራን የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡
የቃሲም ሶሌይማኒ አስከሬን ዛሬ ታህሳስ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ከባግዳድ ቴህራን ሲደርስ ስፍር ቁጥር የሌለው የሀገሪቱ ህዝብ ወደ አደባባዮች ወጥቶ አስከሬኑን ተቀብሏል፡፡
ትናንት በባግዳድም በርካታ ህዝብ ወጥቶ ‘ሞት ለአሜሪካ’ በማለት አሜሪካን የሚዘልፉ መፈክሮችን በማሰማት ለጦር መሪው አስከሬን አሸኛኘት አድርጓል፡፡
የግለሰቡን መገደል ተከትሎ የኢራን ዛቻ ያላማራት አሜሪካ፣ 3000 ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ስትልክ፣ በኢራቅ የሚኖሩ ዜጎቿ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡም አስጠንቅቃለች፡፡
የትራምፕን ከኢራን ጋር ወደ ከረረ አቋም መግባት እና ሌሎች ውሳኔዎች በመቃወም፣ ኒው ዮርክ፣ ዋሺንግተን ዲሲ እና ቺካጎን ጨምሮ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች፣ ጦርነት አንፈልግም ያሉ አሜሪካዊያን ሰልፍ አድርገዋል፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ