የአሜሪካ የመንገደኞች አውሮፕላን ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ ወንዝ ውስጥ ገባ
60 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው የኤሜሪካ ኤርላይንስ አውሮፕላን በሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ለማረፍ ሲቃረብ ነው አደጋው ያጋጠመው
ወንዝ ውስጥ ከገባው አውሮፕላን መንገደኞችን የማውጣት ርብርብ እየተደረገ ነው ተብሏል
የአሜሪካ የመንገደኞች አውሮፕላን ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ ወንዝ ውስጥ ገባ።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤፍኤ) እንዳስታወቀው፥ የአሜሪካ ኤርላይንስ አካል የሆነው ፒኤስኤ ኤርላይንስ ቦምባርዲየር ሲአርጄ 700 አውሮፕላን በዋሽንግተን ዲሲ ሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ ነው ከአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር ጋር የተጋጨው።
60 መንገደኞች እና አራት የበረራ ቡድን አባላትን ያሳፈረው አውሮፕላን ከግጭቱ በኋላ በፓቶማክ ባህር ውስጥ መግባቱም ተገልጿል።
ጥልቅ ዋናተኞች ባህር ውስጥ የገቡትን መንገደኞች ለማውጣት ርብርብ እያደረጉ መሆኑና እስካሁን 18 ሰዎችን ማውጣት መቻላቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
እስካሁን በአደጋው የምን ያህል ሰዎች ህይወት እንዳለፈና የግጭቱ መንስኤ አልታወቀም።
ሪፐብሊካኑ ሴናተር ቴድ ክሩዝ በኤክስ ገጻቸው በአደጋው የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ቢጠቅሱም ምን ያህል እንደሆኑ አላብራሩም።
የአሜሪካ ኤርላይንስ ባወጣው መግለጫ አውሮፕላኑ ከዊቺታ ካንሳስ ተነስቶ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እየበረረ እንደነበር ገልጿል።
አደጋውን ተከትሎ የሮናልድ ሬገን ኤርፖርት ሁሉንም በረራዎች ያቆመ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቹ የነፍስ አድን ስራ ላይ እንዲሰማሩ አድርጓል ብሏል ሲኤንቢሲ በዘገባው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በአሰቃቂው አደጋ" ዙሪያ ገለጻ እንደተደረገላቸውና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እያደረጉት ያለውን ጥረት ማድነቃቸውም ተዘግቧል።
ከመንገደኞች አውሮፕላኑ ጋር የተጋጨው የአሜሪካ ጦር ብላክ ሃውክ ሄሊኮፕተር ሶስት ወታደሮችን አሳፍራ እንደነበር ከመገለጹ ውጪ በአደጋው ምን እንደገጠማቸው እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤፍኤ) የመንገደኞች አውሮፕላን እና ሄሊኮፕተር ግጭቱን መንስኤ ከብሄራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ጋር እንደሚመረምር አስታውቋል።