ከባቢ አየርን ላለመበከል የአውሮፕላን በረራ ሰርዞ ከስራ የታገደው ሰራተኛ ካሳ እንዲከፈለው ተወሰነለት
ሰራተኛው በካሳ መልክ ከሚሰጠው ላይ 75 ሺህ ዩሮ ለአየር ንብረት ለውጥ ተቋማት እለግሳለሁ ብሏል
ቀጣሪው ድርጅት ሰራተኛውን ባስቸኳይ ከፊልድ ስራው በአውሮፕላን እንዲመለስ ያስተላለፍኩትን ትዕዛዝ ጥሷል በሚል ከስራ አግዶት ነበር
ከባቢ አየርን ላለመበከል የአውሮፕላን በረራ ሰርዞ ከስራ የታገደው ሰራተኛ ካሳ እንዲከፈለው ተወሰነለት።
ዶክተር ጊያንሉቻ ግሪማልዳ በዜግነት ጣልያናዊ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪም ነው።
በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የኬል ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሆኖ የተቀጠረው ይህ ሰው ለስራ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ፓፓ ኒው ጊኒ ይላካል።
የፓፓኒው ጊኒ ዜጎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ጋር እንዴት እየኖሩ ነው? ከጉዳቱ ለማገገምስ ምን አይነት መንገዶችን ቢከተሉ የተሻለ ነው የሚል ጥናት ለማካሄድ ነበር ሰራተኛው ወደ ስፍራው የተላኩት።
ይሁንና ሰራተኛው ስራውን አጠናቆ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት መገኛ ጀርመን እንዲመለስ ቢታዘዝም የአውሮፕላን በረራ ወደ ከባቢ አየር በካይ ጋዝ ከሚለቁ የትራንስፖርት አይነቶች አንዱ ነው በሚል ጉዞውን እንደማይቀበል ያሳውቃል።
ተመራማሪውም ከአውሮፕላን ይልቅ ሌላ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ መንገድን መርጦ ወደ ተቋሙ ማምራቱ ተገልጿል።
ተቋሙም ሰራተኛውን ሁለት ወር ዘግይተህ መጥተሀል በሚል ከስራ እና ከደመወዝ ያገደ ሲሆን ሰራተኛው ጉዳዩን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል።
ሰራተኛውም በተባለበት ጊዜ ያልመጣው ለአካባቢው በመቆርቆር፣ በቪዛ፣ በጽጥታ እና ሌሎች ከአቅሙ በላይ በሆኑ ምክንያቶች መሆኑን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ፍርድ ቤቱም ሰራተኛው ያላግባብ ከስራ መሰናበቱ ትክክል እንዳልሆነ የወሰነ ሲሆን ለደረሰበት ጉዳትም ቀጣሪው ተቋም የ75 ሺህ ዩሮ ካሳ እንዲከፈለው ውሳኔ አስተላልፏል።
ዶክተር ጊያንሉቻም በካሳ መልክ ያገኘውን ገንዘብ ለአካባቢ ጥበቃ ተቋማት እንደሚለግስ ተናግሯል።