በአውሮፕላን ማረፍያዎች አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ለልብ ህመምና ስትሮክ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናት አመላከተ
ከአውሮፕላኖች የሚወጣ ድምጽ የሰዎችን የልብ ጡንቻዎች በማጥበብ ደም የመርጨት አቅማቸውን ይቀንሰዋል ተብሏል
ከፍተኛ ድምጽ የሚለቁ አውሮፕላኖች በምሽት ከመብረር ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተመራማሪዎች መክረዋል
በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ለህይወት አስጊ ለሆኑ የልብ ህመሞች እና ለስትሮክ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ጥናት አመላክቷል፡፡
የአውሮፕላን ድምጽ ከሚመከረው መጠን በላይ በሆነባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የልብ ጡንቻዎች ጠባብ እና ደካማ በመሆናቸው በሰውነት ውስጥ ደም የመርጨት አቅማቸው እንደሚዳከም የለንደን ዩኒቨርስቲ የልብ እና የመተንፈሻ አካላት ኮሌጅ ይፋ ያደርገው ጥናት ጠቁሟል፡፡
በተለይም በምሽት ላይ የሚኖሩ ከፍተኛ የአውሮፕላን ድምጾ የሰዎችን የእንቅልፍ ስርአት በማዛባት ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያዙ የጤና እክሎችን ያስከትላል ነው ያለው፡፡
ለአውሮፕላን ጫጫታ የተጋለጡ አይጦች የደም ግፊት መጨመር እና የጭንቀት ሆርሞኖች በሰውነት ውስጥ መበራከት እንደታየባቸው ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ቀጥሎም በአውሮፕላን ማረፍያዎች አቅራቢያ በሚገኙ 3635 ሰዎች ላይ የተደረገው ሙከራ ተመሳሳይ ውጤትን አሳይቷል፡፡
የእነዚህ ልምዶች መደጋገም የረዥም ጊዜ የጤና ቀውሶችን እንደሚያስከትሉ የገለጹት ተመራማሪዎች፥ የደም ግፊት፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች እንዲሁም ስትሮክን የመሳሰሉ የጤና ስጋቶች በነዚህ ሰዎች ላይ መደቀኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ ኮሌስትሮል እንዲከማች እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጤና ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ ከመንግስት እና ከአቪየሽን ኢንዱስትሪው የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ጥናቱን ያጠኑት ተመራማሪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ ድምጽ የሚለቁ የካርጎ እና ሌሎች ግዙፍ አውሮፕላኖች ሰዎች በሚተኙበት ምሽት ሰአት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተገደበ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፕላን ድምጽ በቀን በአማካይ 45 ዴሲባል እና በምሽት ደግሞ በአማካይ ከ40 ዲሲባል እንዳይበልጥ ይመክራል።