የ3 አመቷን ፍልስጤማዊ ህጻን በውሀ አፍና የመግደል ሙከራ ያደረገችው የቴክሳስ ነዋሪ በፖሊስ ተያዘች
የ42 አመቷ አሜሪካዊት በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ህጻኗን በመድፈቅ በመግደል ሙከራ ወንጀል ተከሳለች
በአሜሪካ የጸረ ሴማዊነት እና እስልምና ጠል ወንጀሎች መበራከታቸውን የሀገሪቱ የደህንነት ተቋማት ማስታወቃቸው ይታወሳል
የቴክሳስ ነዋሪ የሆነችው ኤልዛቤት ወልፍ የተባለች ግለሰብ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ በጨዋታ ላይ የነበረች የሶስት አመት ፍልስጤማዊት ህጻን በውሀ አፍኖ የመግደል ሙከራ በማድረግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
የ43 አመቷ አሜሪካዊት ጥቃቱ የደረሰባት የሶስት አመት ህጻን ፣ወንድሟ እና እናታቸው በመኖርያ አፓርትመንታቸው ስር በሚገኝ መዋኛ ገንዳ ውስጥ እየተዝናኑ ባሉበት ነው ወንጀሉን የፈጸመችው፡፡
ግለሰቧ በዋና ገንዳ አካባቢ ወደ ሚገኙት እናት ልጆች ከተጠጋች በኋላ እናትየውን ከየት እንደመጡ ትጠይቃለች፤ ኤች በሚል ስያሜ የተገለጸችው እናት ከፍልስጤም እንደመጡ ነገር ግን የአሜሪካ ዜግነት እንዳላቸው እየነገረቻት ባለችበት ቅጽበት በቅርቧ ያገኝቻትን ህጻን ወደ ገንዳው ውስጥ ይዛ በመግባት አፍና ለመግደል ስትሞክር የህጻኗ እናት የልጇን ህይወት መታደግ ችላለች፡፡
ግለሰቧ ድርጊቱን ከመፈጸሟ በፊት ጥቃት የደረሰባት ህጻን ወንድም የሆነ የ6 አመት ታዳጊ ወደ ውሀ ውስጥ ለመወርወር ጥረት ስታደርግ እንደነበር የልጆቹ እናት ለፖሊስ ተናግራለች፡፡
ኤልዛቤት ወልፍ የተባለችው አሜሪካዊት ድርጊቱን ከፈጸመች በኋላ ሙስሊም ጠል የሆኑ እንዲሁም ሌሎች የዘረኝነት ስድቦችን መሳደቧን የአይን ምስክሮች ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን “ወደ መጣችሁበት ተመለሱ” እያለች በተደጋጋሚ ስትጮህ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ኤች በሚል ስያሜ የተገለጸችው የህጻናቱ ወላጅ እናት “የመጣነው ከፍልስጤም ቢሆንም የአሜሪካ ዜጎች ነን፤ ሀገሬ በጦርነት ውስጥ ትገኛለች እኛ ደግሞ እዚህ ቀን በቀን ጥላቻን እናስተናግዳለን ልጆቼን የት ወስጄ ባሳድግ ደህንነት እንደሚሰማኝ አላውቅም” ስትል ተናግራለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በድርጊቱ የተደናገጡት ህጻናት ከቤት ውስጥ መውጣት እንደማይፈልጉ እና አጋጣሚው በፈጠረባቸው ስነልቦናው ጫና ጤናማ እንቅልፍ ከተኙ ቆይተዋል ብላለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ የምትገኝው ድርጊቱን የፈጸመችው አሜሪካዊት በዋስትና እንድትለቀቅ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን ፖሊስ ዋስትናው የሚፈቀድላት ከሆነ የማስያዥያ ገንዘቡ ከፈተኛ እንዲሆን ጠይቋል፡፡
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በአሜሪካ እስልምና ጠል እና ጸረ ሴማዊነት እንቅስቃሴዎች መጨመራቸውን የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የጥላቻ ወንጀሎች ቁጥርም ማሻቀቡ ነው የተነገረው፡፡