የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ደቡብ ኮሪያ ደረሰች
ዋሽንግተን “ቲወዶር ሮዝቬልት” የተሰኘችውን ግዙፍ መርከብ የላከችው የሴኡልና ፒዮንግያንግ ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በዚህ ወር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ያደርጋሉ
በኒዩክሌር ሃይል የምትሰራው የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ደቡብ ኮሪያ ደረሰች።
“ቲወዶር ሮዝቬልት” የተሰኘችው ግዙፍ መርከብ በዛሬው እለት በደቡብ ኮሪያዋ የወደብ ከተማ ቡሳን መድረሷን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ የጦር መርከብ ደቡብ ኮሪያ የደረሰችው ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ወታደራዊ ትብብራቸውን የሚያጠናክር ስምምነት ከደረሱ ከቀናት በኋላ ነው።
ስምምነቱ ስጋት ደቅኖብኛል ያለችው ሴኡል ከዋሽንግተን እና ቶኪዮ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መክራለች።
የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት በስልክ ባደረጉት ምክክርም የኪምና ፑቲን ወታደራዊ ትብብር የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ያባብሳል በሚል የሶስትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ መስማማታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ከ24 አመት በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ ያቀኑት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ልታስታጥቅ ትችላለች ማለታቸውም ሴኡልና አጋሮቿን አስቆጥቷል።
የሩሲያን አምባሳደር ለማብራሪያ የጠራችው ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አደርጋለሁ የሚል ዛቻ ማሰማቷን ተከትሎም ፑቲን ሴኡል “ትልቅ ስህተት” እንዳትሰራ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
የሁለቱ ኮሪያዎች ውጥረት ባየለበት ወቅት የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ደቡብ ኮሪያ ያቀናቸው በዚህ ወር ለሚካሄድ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ነው ተብሏል።
ልምምዱ የሰሜን ኮሪያ የደህንነት ስጋት በጋራ ለመመከት ያለመ መሆኑ የተጠቀሰ ቢሆንም፥ ቻይና ላይም ትኩረት እንደሚያደርግ ነው የተነገረው።
ሶስቱ ሀገራት በደቡባዊ ቻይና ባህር “ጸብ አጫሪ ድርጊት” በመፈጸም ላይ ናት በሚሏት ቤጂንግ ላይ የጋራ አቋም ይዘው ከነሃሴ 2023 ጀምሮ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መጀመራቸው ይታወሳል።