“ዮም አል አርድ” - ፍልስጤማውያን ለ48 አመታት ያከበሩት የመሬት ቀን መነሻው ምንድን ነው?
እለቱ የእስራኤልን የመሬት ወረራና ዘረፋ ተቃውመው አደባባይ በመውጣታቸው የተገደሉ ፍልስጤማውያን ይታሰብበታል
እስራኤል ከግማሽ ምዕተ አመት በኋላም የፍልስጤማውያንን መሬት መንጠቅና የሰፈራ ቤቶች ግንባታዋን ማጠናከር ተያይዛዋለች
ፍልስጤማውያን በየአመቱ መጋቢት 30ን የመሬት ቀን ወይም “ዮም አል አርድ” ብለው አስበው ይውላሉ።
እለቱ በ1976 በዚሁ ቀን በተነሳ ተቃውሞ ህይወታቸውን ያጡ ፍልስጤማውያን ታስበው የሚውሉበት ነው።
በእስራኤልና በሀይል በተቆጣጠረቻቸው መሬቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን ተቀናጅተው የቴል አቪቭን የመሬት ወረራ መቃወም የጀመሩት መጋቢት 30 1976 ነበር።
በእለት አደባባይ የወጡና ያልታጠቁ ስድስት ፍስጤማውያን መገደላቸውንና ከ100 በላዩ መቁሰላቸውን የዘ ናሽናል ዘገባ ያወሳል።
እስራኤል በገሊላ 2 ሺህ ሄክታር የፍልስጤማውያን መሬትን መውረሷም የተቃውሞው መነሻ እንደነበር ይነገራል።
በእስራኤል የተወረሰው መሬት 3 ሺህ የእግርኳስ ሜዳዎችን ያህል ስፋት አለው።
ፍልስጤማውያን በመሬት ቀን ምን ያደርጋሉ?
በእስራኤልና በሃይል በያዘቻቸው ዌስትባንክና ምስራቅ እየሩሳሌም የሚገኙ ፍልስጤማውያን እለቱን የእስራኤልን የመሬት ወረራ በአደባባይ በመቃወም እና ከመሬቱ ጋር ያላቸውን ትስስር ለማሳየት የወይራ ዛፍ በመትከል ያስቡታል። እለቱ በየአመቱ ሲታሰብ አደባባይ የወጡ ፍልስጤማውያን በእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች ድብደባና ግድያ ሲፈጸምባቸው ይታያል።
የመሬት ቀን የእስራኤልን የመሬት ወረራ አስቁሟል?
እስራኤል ከ48 አመት በፊት 2 ሺህ ሄክታር መሬት በአንድ ቀን እንደወረሰችው አሁንም ወታደራዊ ቀጠና፣ የመንግስት መሬት የሚሉና ሌሎች መጠሪያዎች እየሰጠች የፍልስጤማውያን መሬት በመውሰድ ላይ ናት።
በያዝነው መጋቢት ወር እንኳን በዌስትባንክ 800 ሄክታር መሬት የመንግስት መሬት እንዲሆን በመወሰን ወደራሷ ጠቅልላለች።
በዚህ መሬት ላይም የሰፈራ ቤቶች እና የንግድ ህንጻዎች እንደሚገነቡ የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛለል ስሞትሪች መናገራቸው ይታወሳል።
ቴል አቪቭ በቅርቡም በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ከ3 ሺህ 400 በላይ የሰፈራ ቤቶችን ለመገንባት የወጣውን እቅድ ማጽደቋ አይዘነጋም።
ከጥቅምት 2022 እስከ ህዳር 2023 ባለው ጊዜ ብቻ እስራኤል በሃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም መሬቶች ላይ በጥቂቱ 24 ሺህ ህገወጥ ቤቶች እንዲገነቡ ፈቃድ መስጠቷን የፍልስጤማውያን የመብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክም እስራኤል ክብረወሰን በሆነ መልኩ እያካሄደችው ያለው የሰፈራ ፕሮግራም የፍልስጤምን ሀገር የመሆን ጥረት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከከፈተች ወዲህም የመሬት ወረራና የሰፈራ ቤቶች ግንባታው የጸጥታ ሃይሉን ከማጠናከር እኩል ለቀጣይ ደህንነቴ ወሳኝ ነው ብላ በስፋት እየሰራችበት ነው።