“የኩባ ንግስት” በመባል የምትታወቀው ሰላይ ከእስር ተለቀቀች
አና ሞንተስ አሜሪካዊ ብትሆንም ለኩባው ፊደል ካስትሮ ስትሰልል ተደርሶባት ነበር የእድሜ ልክ ፍርድ የተፈረደባት
በ40 ዓመቷ ታስራ የነበረችው ሞንተስ ከ20 ዓመት እስር በኋላ ተለቃለች
የኩባ ንግስት በሚል የምትታወቀው ሰላይ ከእስር ተለቀቀች።
ሙሉ ስሟ አና ብሌን ሞንተስ ትባላለች። የዘር ሀረጓ ከፑሪቶ ሪኮ ደሴት የሚመዘዝ ቢሆንም እድገቷ እና ህይወቷ ሙሉ አሜሪካዊ ያደርጋታል።
በጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ እየተማረች ሳለች የአሜሪካ የስለላ ተቋም ወታደራዊ ሚስጢሮችን እንድትሰልል ተመለመለች።
በትምህርቷ ጎበዝ ተማሪ መሆኗ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላት እውቀት የደህንነቶችን ትኩረት እንደሳበችም ይነገራል።
ይሄን ተከትሎም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ራስ ምታት የነበሩት የወቅቱ የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮን እና አጠቃላይ ኩባን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንድትሰልል ሀላፊነቱ ለአና ሞንተስ ተሰጥቶ እንደነበር ሮይተርስ ዘግባል።
አሜሪካ በኩባ ፍላጎቶቿን ለማስጠበቅ ያቀደቻቸው በርካታ ውጥኖች ከመሳካት ይልቅ ከሽፈውባታል ተብሏል።
ለእቅዶቹ መክሸፍ ደግሞ አና ሞንተስ ለሀገሯ አሜሪካ ከመሰለል ይልቅ ብሔራዊ የዋሸንግተንን ሚስጢሮች አሳልፋ ለኩባ ስለሰጠች እንደነበር ተገልጿል።
ይሄንን ተከትሎም ሙሉ ሀላፊነቱ ለተሰጣት አና ሞንተስ ላይ በተደረገው ምርመራ ለበርካታ ዓመታት የዋሸንግተን ሚስጥሮችን ለኩባ ስትሰጥ ነበርም ተብሏል።
በዚህም ምክንያት አና ሞንተስ ከፈረንጆቹ መስከረም 2001 ዓመት ጀምሮ እንደታሰረች በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በፍርድ ቤት በነበረው ክርክር ላይ አና ሞንተስ ለምን የአሜሪካንን ሚስጥር ለኩባ እንደሰጠች ስትጠየቅ " በወቅቱ ነገሮችን ሳይ ኩባ አሳዛኝ ሀገር ናት፣ እኛ የራሳችንን ፖለቲካ እና ባህል ልንጭንባት እንደሆነ ገባኝ፣ የሚረዳትም ማንም አልነበረም በዚህ ምክንያትም ይህችን ሀገር መርዳት አለብኝ የሚል ሞራል ተሰማኝ" ስትል ምላሽ ሰጥታም ነበር ተብሏል።
አሁን ላይ ከእስር የተለቀቀችው ይህች አሜሪካዊት ሰላይ የ65 ዓመት አዛውንት የሆነች ሲሆን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ጥብቅ ክትትል እንዲደረግባትም በፍርድ ቤት እንደተወሰነባት ተጠቅሷል።