የኖርዌይ ፖሊስ “የሩሲያ ሰላይ” ነው ብሎ የጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉ አስታወቀ
የኖርዌይ ፖሊስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ “ህገወጥ ወኪል” ሲሉ ገልጸውታል
ተጠርጣሪው ብራዚላዊ እንደሆነ ቢያስመስልም የኖርዌይ ፖሊስ እውነተኛ ማንነቱ ሩሲያዊ ነው ብሎ ያምናል
የኖርዌይ ፖሊስ በአርክቲክ ትሮምሶይ ከተማ “የሩሲያ ሰላይ” ነው ብሎ የጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡
የኖርዌይ ፖሊስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ሄድቪግ ሞ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ያልተለመደ “ህገወጥ ወኪል” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በትሮምሶ ዩኒቨርሲቲ በተመራማሪነት ይሰራ የነበረው ሰውዬው የብራዚል ዜጋ መስሎ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ እውነተኛ ማንነቱ ሩሲያዊ ነው ብሎ እንደሚያምን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዜናውን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው በኖርዌይ ብሮድካስት ኤንአርኬ ነው።
ሄድቪግ ሞ፤ ተጠርጣሪው የ"ብሔራዊ ጥቅም ስጋት" በመሆኑ ከኖርዌይ መባረር አለበት ብለዋል፡፡
ህገወጥ ወኪል (Illegal Agent) ማለት በስውር ሰው የሚወስድ፣ ብዙ ጊዜ የሞተ ሰው ማንነትን የሚጠቀም እንዲሁም ይፋዊ የመንግስት ግንኙነቶች የሌለው የስለላ ሰራተኛ ነው።
እንደ ሞ ከሆነ ተጠርጣሪው ከኖርዌይ መንግስት ኤጀንሲዎች ጋር በመሆን ከ"አርክቲክ ኖርዌይ" ጋር በተገናኘ በ"ትላልቅ ስጋቶች" ዙሪያ በሚሰራው የምርምር ቡድን ውስጥ ተሳትፏል ፡፡
የጥናት ቡድኑ መሪ የሆነው ሰውዬው ለሮይተርስ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው በቅርቡ ከካናዳ ሁለተኛው ዲግሪ ያገኘና በታህሳስ 2021 ትሮምሶ የደረሰ ያልተከፈለው ተመራማሪ ሲሆን ይህም ያልተለመደ ነው ብለዋል፡፡
የኖርዌይ ፖሊስ ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ ሄድቪግ ሞ ማንነቱን ደብቆ የነበረው ሰው እንቅስቃሴ ማስቆም ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው "በርካታ" በዓለም አቀፍ የጸጥታ አካላት ትብብር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ከየትኛው ሀገር እንደሆነ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
"ህገወጥ ወኪል መኖሩ የሩሲያ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው"ም ነው ያሉት ሞ፡፡
የነርዌይ ፖሊስ ይህን ይበል እንጅ የተከሳሹ ጠበቃ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡
በይፋ በተገኘው መረጃ መሰረት የተጠርጣሪው አለቆች በካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የውትድርና፣ የደህንነት እና የስትራቴጂክ ጥናቶች ማዕከል የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
በትሮምሶ ዩኒቨርሲቲ የደህንነት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ጉንሂልድ ሁገንሰን ግጆርቭ "በመጀመሪያ ያገናኘኝ ባለፈው አመት መኸር ነው...እንደሌሎች ተመራማሪዎች ገምግመነዋል። ከእሱ ሪፈረንሶችም አንዱ በደንብ የማውቀው ፕሮፌሰር ነው" ብለዋል፡፡
"በእርግጥም በጣም ደስ ሚል ሰው ነበር በስራው በጣም ጎበዝ ነው" ያሉት ፕሮፌሰሯ "እሱ ስለራሱ ከተናገረው ውጭ ሌላ ነገር ነው ብለን የምንጠረጥርበት ምንም ምክንያት አልነበረንም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኔቶ አባል የሆነችው ኖርዌይ ሩሲያን በአርክቲክ የምትዋሰን ሲሆን ሞስኮ በየካቲት ወር ዩክሬን ላይ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ የጸጥታ ጥበቃዋን እንዳጠናከረች ነው፡፡