34 በመቶ አሜሪካውያን ሩስያን ወዳጅ ሀገር አድርገው እንደሚመለከቱ ከህዝብ የተሰበሰበ አስተያየት ጠቆመ
በሁለቱ ሀገራት ያለው አለም አቀፋዊ ፉክክር አመታትን ቢያስቆጥርም የዩክሬን ጦርነት በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዳባባሰው ይነገራል

ባሳለፍነው አርብ በትራምፕ እና በዘለንስኪ መካከል ከነበረው በግለት የታጀበ ንግግር በኋላ ዩክሬንን የሚደግፉ ሩስያን የሚያወግዙ ሰልፎች በአሜሪካ ተካሂደዋል
በፓርቲ አባላት ወይም ደጋፊዎች እና በትውልድ መካከል አሜሪካውን ለሩስያ ያላቸው አመለካከት የተከፋፈለ መሆኑን ከህዝብ የተሰባሰበ አስተያየት አመላክቷል፡፡
ሲቤኤስ ኒውስ ከሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ዱላ ቀረሽ ውይይት እስከተካሄደበት አርብ ድረስ አሜሪካውያን ለሩስያ ያላቸውን አመለካከት በተመለከተ የህዝብ አስተያየት ሰብስቧል፡፡
በዚህ መሰረት 34 በመቶ አሜሪካውያን ሩስያን እንደ አጋር ወይም ወዳጅ ሀገር አድርገው ሲመለከቱ ፣ 32 በመቶ ያህሉ ወዳጅ ያልሆነ ሀገር ፣ 34 በመቶዎች ደግሞ ጠላት አድርገው እንደሚመለከቷት ዘግቧል፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ከዴሞክራቶች በተሻለ ለሩስያ መልካም አስተያየት ያላቸው ሲሆን 41 በመቶ የፓርቲው ደጋፊዎች ሩስያን አጋር ሀገር አድርገው እንደሚቆጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሁለቱ ሀያላን ሀገራት ሩስያ እና አሜሪካ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ፣ የወታደራዊ ፣ የጂኦፖለቲካዊ እና የርዕዮተ አለም የበላይነት ፉክክር በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡
የሀገራቱ ውጥረት በሶቭየት ህብረት እና በቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በአመታት ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች ውጥረቱ አንድ ጊዜ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ረገብ እያለ ቀጥሏል፡፡
በ2022 የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ የጆ ባይደን አስተዳደር ከሞስኮ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት አቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዋሽንግተን ለዩክሬን ባሳየችው ውግንና ሁለቱ ሀገራት ለጦር መሳሪያ መማዘዝ የሚያቀራርብ ውጥረት ውስጥ ቆይተዋል፡፡
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሲቢኤስ ኒውስ የህዝብ አስተያየት 52 በመቶ አሜሪካውን ዩክሬንን እንደሚደግፉ ፣ 44 በመቶዎቹ ገለልተኛ አቋም እንደሚይዙ እና 4 በመቶ ብቻ ከሩሲያ ጎን እንደሚቆሙ አሳይቷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በሩስያ እና ዩክሬን የያዙትን አቋም በተመለከተ 11 በመቶ አሜሪካውን ፕሬዝዳንቱ ኪቭን እንደሚደግፉ የሚያምኑ ሲሆን፤ 46 በመቶዎቹ ግን ሞስኮን እንደሚወዱ ያምናሉ፤ሌሎች 43 በመቶ የሚሆኑት ትራምፕ ሁለቱንም ሀገራት በእኩልነት ያስተናግዳሉ ብለዋል፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ በመጋቢት 2024 ባሰባሰበው ተመሳሳይ የህዝብ አስተያየት 37 በመቶ አሜሪካውያን ሩስያ የሀገራቸው ጠላት እንደሆነች ሲናገሩ 3 በመቶ የሚሆኑት ወዳጅ ሀገር እንደሆነች ሀሳባቸውን ገልጸዋል ነበር፡፡