ከዩክሬን ጦርነት በድብቅ ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙ 5 ሀገራት እነማን ናቸው?
ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት የአለምን ጂኦፖለቲካዊ አሰላለፍ የቀየረ እነደሆነ ይነገራል

ጦርነቱን አምስት ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖን ለማግኘት ተጠቅመውበታል
ሩስያ ከሶስት አመት በፊት ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በሚል የዩክሬንን ድንበር አቋርጣ የጀመረችው ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡
አሜሪካ እና አውሮፓውያን እንዲሁም አንዳንድ የእስያ ሀገራት ለዩክሬን በመቶ ቢሊየን ዶላር የሚቆጠር የጦር መሳሪያ ፣ የገንዘብ እና ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
ሩስያ በበኩሏ ህንድ ፣ ቻይና ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራንን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ አጋርነቷን በማጠናከር የምዕራባውን እና አሜሪካን ተጽዕኖ ለመቋቋም ጥረት አድርጋለች፡፡
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀድሞው አስተዳደር በተለየ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን እያደረጉ ነው፡፡
ጦርነት ወደ አለም አቀፋዊ የጂኦፖለቲካዊ ግጭት መቀየሩ እየተነገረ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን ሀገራት ተጽዕኗቸውን ለማጎልበት ወርቃማ እድል ሆኖላቸዋል።
ሚሊታሪ ወች መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ይህ ጦርነት ባልተጠበቁ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጥቅሞች የዓለም ኃያላን ሀገሮችን አሰላለፍ እንዴት እንደለወጠው ገልጿል።
ከዩክሬን ጦርነት በድብቅ የሚጠቀሙ 5 ሀገራት እነማን ናቸው?
ቻይና
ጦርነቱን ተከትሎ በሩስያ ላይ በምዕራባውን ከተጣለው ማዕቀብ ባለፈ የጃፓን ፣ የደቡብ ኮሪያ እና የታይዋን ኩባንያዎች ከሩስያ ጋር እንዳይሰሩ መከልከላቸው ሞስኮ በከፍተኛ ደረጃ በቻይና ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጎታል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ፣ ለጦር መሳሪያ እና ለተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶች የሚያገለግሉ ሴሚኮንዳክተሮች በስፋት በማቅረብ በሩሲያ ገበያ ያላቸውን ድርሻ በመጨመር ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል።
ከዚህ ባለፈም አንዳንድ የጦር መሳሪያ እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሩስያ ምድር ቅርንጫፎችን በመክፈት በገበያው ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል፡፡
የምዕራቡ ዓለም ትኩረት በአውሮፓ ግንባር ላይ መሆን ቤጂንግ በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ያላትን ይዞታ እንድታስፋፋ ከማስቻሉም በላይ ሩሲያ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያረገችው ወታደራዊ ትብብር በተዘዋዋሪ የቻይናን ቀጠናዊ ደህንነት ማሻሻሉ ተገልጿል፡፡
ሰሜን ኮሪያ
ከሞስኮ ጋር የወታደራዊ አጋርነት ስምምነትን የፈጸመችው ፒዮንግያንግ በዩክሬን ጦርነት ወታደሮቿን ወደ ሩስያ በመላክ ጭምር እየተሳተፈች እንደምትገኝ ይነገራል፡፡
ከዚህ ባሻጋር ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ በ2024 አጋማሽ ከ6 ሚሊየን በላይ የመድፍ ዛጎሎች እንዲሁም ቡልሳ -4 ፀረ ታንክ ሚሳኤል እና ኬ ኤን-23ቢ የመሳሰሉ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ለሩሲያ በመሸጥ ትልቅ ትርፍ ማስመዝገቧን ሚሊታሪ ወች መጽሄት አስነብቧል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ የተጠናከረው ወዳጅነት ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም እንዳታገኝ ክልከላ ተጥሎባት የነበሩ የጠፈር ሳይንስ ፣ የባህር ሰርጓጅ መርከቦች እና የተዋጊ አውሮፕላኖች የላቁ ቴክኖሎጂዎችን ከሩስያ እንድታገኝ አስችሏታል፡፡
በተጨማሪም ፒዮንግያንግ ከሞስኮ በዝቅተኛ ዋጋ የነዳጅ ዘይት መገብየት እንድትችል፣ በሩስያ ውስጥ ዜጎቿ የስራ እድል እንዲያገኙ እና ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት ጠቅሟታል፡፡
ህንድ
ህንድ የሩስያን የነዳጅ ዘይት በቅናሽ ዋጋ በመግዛት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን እና ተወዳዳሪነቷን በማሳደግ በጦርነቱ ከፍተኛ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አንዷ ሆናለች።
እ.ኤ.አ. በ2023 አጋማሽ ላይ ህንድ ከውጭ ሀገራት ከምታስገባው ነዳጅ 46 በመቶውን የሚሸፍነው ከሞስኮ የምትገዛው ነዳጅ ነው፤ ከጦርነቱ በፊት ደልሂ ከሞስኮ የምትገበየው ነዳጅ ከ 2 በመቶ ያነሰ ነበር፡፡
ጦርነቱ ህንድ በአሜሪካ ዶላር ላይ የነበራትን ጥገኝነት እንድትቀንስ ከማድረጉም ባለፈ የሩፒ፣ ሩብል እና ዩዋን ግብይት ማደግ በሶስቱ ሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲጨምር ምክንያት ነው።
ኢራን
ከሶቪየት ህብረት ውድቀት በኋላ ሩሲያ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች፤ ሆኖም በዩክሬን ጦርነት ጊዜ የሀገራቱ ግንኙነት ያደገውን ያህል አልነበረም፡፡
ቴሄራን ከመስከረም 2022 ጀምሮ በጦርነቱ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት ሻሄድ-136 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለሩስያ ገበያ አቅርባለች፡፡
ቴህራን በ2025 ለማድረስ የታቀዱትን ሱ-35 ተዋጊ ጄቶችን የመሳሰሉ የሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን በመግዛት የመካለከያ ኢንዱስትሪዋን አቅም እና ትርፍ ለማሳደግ የዩክሬን ጦርነት በር ከፍቶላታል፡፡
በሌላ በኩል የአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መጨመር የኢራን መንግስት ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል። ይህም የምዕራባውያን ማዕቀቦችን በመጋፈጥ ኢኮኖሚያዊን ለመደጎም አቅም አላብሷታል፡፡
ቱርክ
ጦርነቱ እየተፋፋመ ሲመጣ ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቷቸውን የስንዴ ፣ ጥራጥሬ እና የምግብ ዘይት ግብአቶችን በጥቁር ባሕር ላይ እንዲያሳልፉ በማሸማገል ቱርክ በዲፕሎማሲው መድረክ ወደ ፊት የመጣችበትን አጋጣሚ አግኝታለች፡፡
ከዚህ ባለፈም የዩክሬን እና የሩስያ ባለሀብቶች ማረፍያ በመሆን ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነችው አንካራ ከፍተኛ የቅንጦት ንብረቶች ሽያጭ ገበያ ደርቶላታል፡፡
የመከላከያ ኢንደስትሪውም ቢሆን ለዩክሬን የድሮን እና ሌሎች የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል።