
የአሜሪካ ፖለቲከኞች ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለቦታው አይመጥኑም የሚል ሀሳቦችን እያንሸራሸሩ ይገኛሉ
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እኔን መተካት ከባድ ነው አሉ፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ከሰሞኑ ወደ ዋሸንግተን አቅንተው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የተለያዩ ሀሳቦች እየተሰሙ ይገኛል፡፡
የማዕድን ስምምነት ለማድረግ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ያቀኑት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ጋር ከተጋጩ በኋላ ዳግም ስምምነቱን ለመፈረም ዝግጁ ነኝ ቢሉም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ከዋሸንግተን ወደ ለንደን ያመሩት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከአሜሪካ ፖለቲከኞች የተነሳባቸውን የስልጣን ማስረከብ ጥያቄ ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በምላሻቸውም “እኔን መተካት ቀላል ሊሆን አይችልም፣ ነገር ግን ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶ አባል ከሆነች ተልዕኮዬ ተሳክቷል ማለት ነው፡፡ እኔም በምትኩ ስልጣን ልለቅ እችላለሁ” ብለዋል፡፡
“እኔን በሌላ መሪ ለመተካት በዩክሬን ምርጫ ማካሄድ በቂ አይሆንም፣ የግድ ከእኔ ጋር መደራደር እና በምርጫው እንዳልሳተፍ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የደህንነት አማካሪ የሆኑት ማይክ ዋልዝ ለሲኤንኤን እንዳሉት “ከሩሲያ እና ከእኛ ጋር መደራደር የሚችል እና ጦርነቱን ማስቆም የሚፈልግ መሪ ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ የሆኑት ማይክ ጆንሰን በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ወደ ቀልቡ ሲመለስ አልያም ሌላ መሪ ጦርነቱ ስለሚቆምበት ሁኔታ መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡